ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በዓባይ ግድብ ዙሪያ የምክክር መድረክ አዘጋጅቻለሁ አለች፡፡

የኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ በኪንሻሳ ይገናኛሉ መባሉን አልጀዚራ ጽፏል፡፡

የፊታችን ቅዳሜ ይጀመራል የተባለው የሶስቱ ሀገራት ምክክር ለ 3 ቀናት እንደሚቆይ ተገልጿል፡፡

በዉይይቱ ላይ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማትም ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የህዳሴ ግድቡ አሞላልን በተመለከተ ግብጽና ሱዳን በተለያዩ ጊዜያት እየፈጠሩ ባሉት ውዝግብ አሁንም ድረስ መግባባት ላይ እንዳልተደረሰ ይታወቃል፡፡

ኢትዮጵያም የህዳሴ ግድቡን ውሀ ከመሙላት የሚያግዳት ምንም ሀይል እንደሌለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በምክር ቤት ባደረጉት ንግግራቸው ማሳወቃቸው ይታወሳል፡፡

የግብጹ ፕሬዝደንት አብደል ፈታህ አል ሲሲ ከሰሞኑ ማንም ከግብጽ አንድ ጠብታ ውሃ ሊወስድ አይችልም፤ ማንም ይህንን መሞከር ከፈለገ ያድርገው፤ ይህ ግን አካባቢውን ያናጋል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሚቀጥለው የክረምት ወቅት 13.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ መሙላቷን እንደማታቆም በተደጋጋሚ የተናገረች ሲሆን፤አሁንም ድረስ ከዚህ አቋሟ አላፈገፈገችም፡፡

የህዳሴዉ ግድብ ግንባታ 79 በመቶ መጠናቀቁን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ሁለተኛ ዙር የዉሃ ሙሌት ለማከናወንም ከወዲሁ ዉሃዉ የሚተኛበትን ቦታ ምንጣሮ ለማከናወን እየተዘጋጀች መሆኑን ኢትዮጵያ አሳዉቃለች፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
በመቅደላዊት ደረጀ
መጋቢት 23 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.