ፍልሰተኛ አካል ጉዳተኞች ይበልጥ ለከፋ ችግር እየተዳረጉ መሆኑን ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት አስታወቀ፡፡

አለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ወይም IOM በዓለማችን ከአስር ፍልሰተኞች አንዱ አካል ጉዳተኛ መሆኑን በጥናቴ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

በፍልሰት ላይ አካል ጉዳተኛነት ሲታከልበት የስራ ዕድል ማጣት፣ የጤና አገልግሎት ለማግኘት መቸገር እንዲሁም ለማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ቀውስ መዳረግን እያስከተለ መሆኑንም ድርጅቱ ገልጿል፡፡

ይህን ተከትሎ አለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት በቱርክ ከሚገኘዉ የመንግስታቱ ድርጅት የህዝብ ጉዳዮች ኤጀንሲ አጋርነት ማህበር ጋር በመተባበር ለአካል ጉዳተኛ ፍልሰተኞች የሚውል የልዩ ድጋፍ መርሃ ግብር አስተዋዉቀዋል፡፡

መርሃግብሩ በአውሮፓ ህብረት የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት ሲሆን በቱርክ የሚገኙ ፍልሰተኞችን ለመደገፍ ያለመ ነው ተብሏል፡፡

ቱርክ አራት ሚሊዬን የሚሆኑ ፍልሰተኞችን በማስጠለል ከአለም በቀዳሚነት ትቀመጣለች።

በሃገሪቱ ከሚገኙት 4 ሚሊዮን ፍልሰተኞች መካከልም 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ያህሉ ሶሪያውያን መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በቱርክ ከሚገኙ አካል ጉዳተኛ ፍልሰተኞች መካከልም ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት የዚች ችግር ሰለባ ሆነው ተገኝተዋል ተብሏል፡፡

ታዲያ አዲሱ የልዩ ድጋፍ መርሃግብር ለአካል ጉዳተኞች እና በአቅራቢያቸው ለሚገኙ ፍልሰተኞች የስነ-ልቦና ድጋፍ፣ የህግ ምክር አገልግሎት፣ ከጾታዊ ጥቃት መጠበቅ እና መሰል ድጋፎችን በቱርክ እንዲያገኙ ያስችሏቸዋል መባሉን አናዶሉ ዘግቧል፡፡

በመቅደላዊት ደረጀ
መጋቢት 24 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *