የካቲት ወር ላይ ቅርስ የሚጠግኑ ባለሙያዎችን አሰልጥኖ ሚያዝያ ወር ላይ ለላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጥገና ይደረጋል ተብሎ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ጥገናው በተባለዉ ጊዜ እንደማይጀመር ኢትዮ ኤፍ ኤም ሰምቷል፡፡
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳረጋገጡት፣ ፈረንሳይ በኮቪድ 19 ምክንያት ሀገሯን ዘግታለች፤በዚህም ከፈረንሳይ ይመጣሉ ተብለው የነበሩ የቅርስ ጥገና ባለሙያዎች ሊመጡ አልቻሉም ነዉ ያሉት፡፡
የካቲት ወር ላይ የቅርስ ጠጋኝ ባለሙያዎች ስልጠና የተሰረዘውም በዚህ ምክንያት ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ለማደስ ቃል የገባችው ፈረንሳይ መግቢያ መውጫ በሮቿን ስትከፍት በንግግር ውሳኔዎች ይወሰናሉ ተብሏል፡፡
የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት አናት ላይ ቅርሱን ከዝናብ እና ፀሃይ ይከላከላል ተብሎ በዩኔስኮ እና በጣሊያን መንግስት የተከለለው መጠለያ፣ ለቅርሱ አደጋ ሆኗል እየተባለ በተለያየ ጊዜ ከአካባቢው ነዋሪና ከአስተዳደሩ ቅሬታ ይነሳል፡፡
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኤማኑኤል ማክሮን ጉብኝት ለማድረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅት ጉብኝታቸውን የጀመሩት ከላሊበላ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ለማስጠገን ቃል ከገቡም ሁለት ዓመታት ቢያስቆጥርም አሁንም በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ጊዜው ተራዝሟል ተብሏል፡፡
በመቅደላዊት ደረጀ
ሚያዝያ 07 ቀን 2013 ዓ.ም
