“…በኢትዮጵያ ላይ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ግንባር ፈጥረው የተነሱበት ወቅት ላይ እንገኛለን” ሲሉ -ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ፥ ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ግንባር ፈጥረው የተነሱባት አገር በመሆኗ ኢትዮጵያን ለማዳን ሁሉም አንድ መሆን ይገባዋል ሲሉ ተናገሩ።

ኢትዮጵያ የውስጥ እና የውጭ ጠላቶች ግንባር ፈጥረው የተነሱበት ወቅት ላይ እንገኛለን ያሉት ጄነራል ብርሃኑ፥ እነዚህ ጠላቶች አገሪቷን በማዳከም ከችግር እንዳትወጣ፣ ታላቅነቷን አስጠብቃ እንዳትሄድ እየሰሩ ነው ብለዋል።

ይህ ሁሉ ትንኮሳ፣ ማናቆር እና ህብረተሰቡን እርስ በእርሱ ማባላት ኢትዮጵያን ለማዳከም ነው ሲሉ ተደምጠዋል። የዚህ ፍላጎት ሀገሪቷ ስትዳከም ባላት ሃብት እንዳትጠቀም ለማድረግ መሆኑ ገልፀዋል።

በዚህም በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች የሚፈጠሩትን ግጭቶች ሰራዊቱ በየቦታው እየሄደ እያመከነ ይገኛል ነው ያሉት። ህዝቡም ከሰራዊቱ ጎን በመቆም የተደገሰውን ለማክሸፍ መታገል ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ፥ “ከ100 ዓመታት ጀምሮ ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚሰሩ ኃይሎች ዛሬ ተጠናክረው አገራችን ላይ ዘምተዋል” ብለዋል። ባንዳዎችን ህብረት ፈጥረው አገር ለማፍረስ እየተንቀሳቀሱ ነው ያሉት ኢታማዦር ሹሙ ፣ እነዚህ ኃይሎች በውጭ ወራሪ ልንረታ እንደማንቻል ስለሚያውቁ ከውስጣችን ሊያፈራርሱን ያስባሉ ሲሉ ተናግረዋል።

ጄኔራል ብርሃኑ፥ “ኢትዮጵያን ለማዳን ሁላችንም አንድ መሆን ይገባናል፤ ተሳስተው የጠላት መሳሪያ የሆኑ አካላትም ቆም ብለው ማሰብ እንደሚገባቸውና ለሃገራቸው ጥፋት እየደገሱ ለሌሎች ታሪካዊ ጠላቶች በር መክፈት የለባቸውም” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ሚያዝያ 26 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *