ከ90 በመቶ በላይ የእንቦጭ አረም ከጣና ሃይቅ ላይ ቢወገድም አረሙ ባለመቃጠሉ ስጋት መፍጠሩ ተነገረ

የጣና ሃይቅን ከእንቦጭ አረም ለመታደግ በተደረገዉ ርብርብ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነዉን አረም ማስወገድ ቢቻልም እስካሁን ድረስ ማቃጠል ባለመቻሉ ስጋት እንደፈጠረበት የጣና ሃይቅና ሌሎች የዉሃ አካላት ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

በኤጀንሲዉ የብዝሃ ህይወት ልማትና ጥበቃ ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ መዝገቡ ዳኘዉ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ፤ ከሃይቁ ላይ አረሙን ማረም ቢቻልም የታረመዉ የእንቦጭ አረም ባለመቃጠሉ ስጋትን ፈጥሯል ብለዋል፡፡

የአየር ሁኔታዉ ዝናባማ በመሆኑ እንዲሁም የበጀት ችግር በመግጠሙ አረሙን ማቃጠል እንዳልተቻለም አቶ መዝገቡ ተናግረዋል፡፡

በሃይቁ ዳርቻ ላይ የተወገደዉ የእንቦጭ አረም ተከማችቶ እንደሚገኝ ያስታወቁት ዳይሬክተሩ፤ ይህም በፍጥነት ማቃጠል ካልተቻለ መልሶ ወደ ሃይቁ የመስፋፋት ዕድል አለዉ ነዉ ያሉት፡፡

በመሆኑም የፌደራልና የክልሉ መንግስት አስፈላጊዉን ድጋፍ በማድረግ በቀጣይ አንድ ወር ዉስጥ አረሙን የማቃጠል ስራ መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የክረምት ወቅት እየተቃረበ በመምጣቱና በነዚህ ወራት ደግሞ አረሙ በስፋት የሚታይበት በመሆኑ ጣናን ለመታደግ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም አቶ መዝገቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም እስካሁን በተሰራዉ የአካባቢ ጥበቃ ስራ ለጣና ሃይቅ ብቻ ተብሎ የተከናወነ ሥራ ባለመኖሩ ከሃይቁ ገባር ወንዞችና ከተፋሰሱ ደለል ወደ ዉሃዉ እየገባ እንደሆነም አንስተዋል፡፡

በመሆንም የክልሉ የግብርና ፤ደንና የአየር ንብረት ለዉጥ ኮሚሽን ከፌደራሉ መንግስት ጋር በጋራ በመሆን የጣን ሃይቅን ገባር ወንዞችና ተፋሰሱን ማልማት እንደሚገባዉ ተነግሯል፡፡

ባጠቃላይ የጣናን ህልዉና ለመታደግ የክልሉ መንግስት፤ የፌደራሉና መላዉ ኢትዮጵያዉያን የእጃቸዉን እንዲዘረጉ ጥሪ ቀርቧል፡፡

በአባቱ መረቀ
ግንቦት 25 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *