የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በመኪና ስርቆት የተጠረጠሩ ግለሰቦችን መያዙን አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በተለያዩ ጊዜያቶች ተሰርቀው የነበሩ 13 ተሽከርካሪዎች ከእነ ወንጀል ፈጻሚዎቹ መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናገሩ፡፡

ወንጀል ፈጻሚዎቹ እና የተሰረቁት ተሽከርካሪዎች የተያዙት ባለፉት ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ሲሆን ፖሊስ ኮሚሽኑ ከያዛቸው ተሽከርካሪዎች መካከል ሁለቱ የሞተር ቁጥራቸውም ሆነ የሻንሲ ቁጥራቸው ሳይቀየር ባሉበት ሁኔታ ተይዘዋል ብለዋል፡፡

ከተያዙት ተሽከርካሪዎች መካከል አብዛኛዎቹ ታርጋ ቁጥራቸው የተቀየረ ሲሆን ድርጊቱም ከጋራዥ ቤቶች ጋር በመተባበር እንዲሁም በጨረታ ከሚሸጡ ተሽከርካሪዎች ላይ ታርጋ ቁጥሮችን በመግዛት የሚለጥፉ እንደሆነ ኮማንደር ፋሲካ ገልጸዋል፡፡

የተቀሩት ግን ውጫዊ አካላቸው ሳይቀር ለውጥ ተደርጎባቸው የተያዙ ሲሆን 11 ተሽከርካሪዎች የሞተር ቁጥራቸው ተቀይሮ መያዛቸውን ኮማንደር ፋሲካው ነግረውናል፡፡

ፖሊስ ኮሚሽኑ ወንጀል ፈጻሚዎቹን ተከታትሎ በመያዝ ለህግ እያቀረበ እንደሚገኝም ያስታወቀ ሲሆን ህብረተሰቡ የተቀጠቀጡ ታርጋ ቁጥሮችን በሚያይበት እና ታርጋ ቁጥር የሚቀይሩ አሽከርካሪዎች በሚያይበት ጊዜ ጥቆማ መስጠት አለበት ሲሉ ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ ተናግረዋል፡፡

ሔኖክ ወ/ገብርኤል
ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *