በህገ ወጥ ንግድ ስራ ላይ በተሰማሩ ከ60 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ መዉሰዱን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡

ቢሮዉ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳስታወቀዉ ባለፉት 10 ወራት በህገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ በነበሩ 60 ሺህ 3 መቶ 45 ነጋዴዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ ወስጃለሁ ብሏል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መስፍን አሰፋ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ፣ የኑሮ ዉድነቱ አዲስ አበባ በሚሰሩ የንግዱ ማህበረሰብ ላይ ህጋዊ እርምጃዎች እየወሰድን ነዉ ብለዋል፡፡

ለዋጋ ንረቱ መባባስ የህገ ወጥ ነጋዴዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ያነሱት አቶ መስፍን ፤በዚህም ከፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እስከ ማገድ ድረስ የሚደርስ እርምጃ ተወስዶባቸዋል ነዉ ያሉት፡፡

በዚህም 1 መቶ 9 ነጋዴዎች ታግደዋል፤ 2 መቶ 18 ክስ ተመስርቶባቸዋል፤ ከ19ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ታሽገዋል ተብሏል፡፡

በተጨማሪም ከ39 ሺህ በላይ በሚሆኑት ላይ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸዉም ምክትል ሓላፊዉ ነግረዉናል፡፡

ባጠቃላይ የኑሮ ዉድነቱ እንዲባባስና የዋጋ ንረቱ እንዲጨምር ሲያደርጉ በነበሩ 60 ሺህ 3 መቶ 45 ነጋዴዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ ተወስዷል፡፡

በአሁኑ ወቅት በከተመዋ የሚስተዋለዉን የኑሮ ዉድነት ለማረጋጋት ከሸማች ህብረት ስራዎች ጋራ በቅርበት እየተሰራ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ መስፍን፣ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ለሸማች ማህበራት በማመቻቸት ወደ ስራ እንደገቡም ታወቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም እንደ አገር ከዉጭ በሚገቡ የዘይት፤ ስንዴ፤ ሩዝ፤ ስኳርና የሕጻናት ወተት ለ6 ወራት ከታክስ ነፃ እንዲገቡ ስለመደረጉም አቶ መስፍን አስታዉሰዋል፡፡

ከህገወጥ ነጋዴዎች በተጨማሪ የምርታማነት ችግርና ኮቪድ 19 ለኑሮ መወደድ የራሳቸዉ አስተዋፅኦ እንዳለቸዉ የተገለፀ ሲሆን፣ ህብረተሰቡ ከሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት እንዲጠቀሙ መክረዋል፡፡

ቢሮዉ ከ1 መቶ ሺህ ኩንታል በላይ የጤፍ ምርት ለሸማች ማህበራት ማከፋፈሉን የተገለጸ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት መንግስት በድጎማ ከዉጭ ያስገባዉን የስንዴ ምርት ከሸማች ስራ ማህበራት በ 2ሺህ 5 መቶ 40 ብር ማግኘት እንደሚቻልም ኃላፊዉ ተናግረዋል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን ቻናላችንን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።

በአባቱ መረቀ
ሐምሌ 15 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *