የኢትዮጵያ የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ቢሮ ቡድን የዓለም የምግብ ድርጅት አውሮፕላን አደጋ ለመመርመር ወደ ስፍራው አቀና

ሐምሌ 20 ቀን ምስራቅ ሀረርጌ አደጋ የደረሰበትን ሴስና ካራቫን የዓለም ምግብ ድርጅት አውሮፕላን የአደጋ መንስኤ ለማጣራት መርማሪ ቡድን ወደ ስፍራው አቀና፡፡

የኢትዮጵያ የአውሮፕላን አደጋ መርማሪ ቢሮ ያዋቀረው ቡድን በዛሬው እለት አደጋው ወደ ደረሰበት ስፍራ አቅንቷል፡፡

የቢሮው ሀላፊ ኮሎኔል አምድዬ አያሌው ለኢትዮ የንግድ እና ኢንቨስትመንት መድረክ እንደገለጹት ንብረትነቷ የአቢሲኒያ የበረራ አገልግሎት የሆነችው እና በአለም የምግብ ድርጅት በኪራይ የሚጠቀምባት ሴስና ካራቫን የምዝገባ ኮድ ET-AMI አውሮፕላን ሁለት አብራሪዎች እና ሁለት መንገደኞች አሳፍራ ከጂጂጋ የተነሳችው ከቀኑ 7 ሰአት ከ13 ደቂቃ ነበር፡፡

ወደ ድሬደዋ 33 ደቂቃ ከበረረች በኋላ 7 ሰአት ከ46 ደቂቃ ላይ ምስራቅ ሀረርጌ ሀሮማያ ኮምቦልቻ ወረዳ ከመለስተኛ አቀበት ጋር ተጋጭታ ወድቃለች፡፡

ሁለት አብራሪዎችና ሁለት መንገደኞች ጉዳት ሳይደርስባቸው ከአውሮፕላኗ እንደወጡ ተገልጿል፡፡

አውሮፕላኗ ከአቀበቱ ጋር ልትጋጭ የቻለችው በወቅቱ በነበረው አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ እንደሆነ ይገመታል፡፡

የኢትዮጵያ የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ቢሮ ያዋቀረው ቡድን በዛሬው እለት ወደ ድሬደዋ መንቀሳቀሱን የገለጹት ኮሎኔል አምድዬ ቡድኑ አደጋው በደረሰበት ስፍራ ተገኝቶ አስፈላጊውን መረጃ ሰብስቦ እንደሚመለሱ ተናግረዋል፡፡

የአደጋ ምርመራ ስራው ሲጠናቀቅ ሪፖርቱ ይፋ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

የአውሮፕላኗ የበረራ መስመር አዲስ አበባ – ዋርዴር – ጂጂጋ – ድሬደዋ እንደነበር ታውቋል፡፡
ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን ቻናላችንን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ሐምሌ 21 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *