አየር መንገዱ “ዲጂታል ስራ ፈጠራና ኢኖቬሽን” በሚል በተካሄደው የዲጂታል ኢትዮጵያ ተከታታይ የበይነ መረብ ውይይት አካል በሆነው መድረክ ላይ ነው ይህንን ይፋ ያደረገው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቢዝነስ ዲቨሎፕመንትና የኢኖቬሽን ሃብ መስራችና ዳይሬክተር አቶ አብይ አስራት የአየር መንገዱ አጋሮች የሚሳትፉበትና ለበረራ ኢንደስትሪው መፍትሄ የሚሆኑ የፈጠራ ስራዎችን ለማልማት የሚያስችል የዲጂታል ስርዓት ከመጪው ነሃሴ ጀምሮ ይፋ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
አጋሮች የፈጠራ ሃሳቦቻቸውን የሚያለሙበት፣ የሚያሳድጉበትና ወደ ምርትና አገልግሎት የሚያውሉበት ስርዓት እንደሚዘረጋና ይህንንም አየር መንገዱ በገንዘብ የሚደግፍበት ስርዓት እንደሚያመቻች ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከደንበኞቹ የፈጠራና የማሻሻያ ሃሳቦችን የሚቀበልበት “የእኔ ሃሳብ” የሚል የዲጂታል ስርዓት በመዘርጋት የተሻሉ ሃሳቦችን ተቀብሎ እውቅና በመስጠት ወደ ስራ እያስገባ ይገኛል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሐመድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጀመረው ለቴክኖሎጂ ስራ ፈጣሪዎች ምቹ ሁኔታን የመፍጠር ተግባር ሌሎች የግል ተቋማትና የልማት ድርጅቶችም ሊከተሉት የሚገባ በጎ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርም ለፈጠራ ልማት ስራዎች የመስሪያ ቦታና ገንዘብ ከሚያመቻቹ ተቋማት ጋር በትብብር ለመስራትና ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ማህበራዊ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን ቻናላችንን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ሐምሌ 22 ቀን 2013 ዓ.ም
