የውጭ አበዳሪዎች ለኢትዮጵያ ብድር ለመልቀቅ እያቅማሙ ነው ተባለ፡፡

ለኢትዮጵያ ዋነኛ አበዳሪ የሚባሉ የፋይናንስ ተቋማት ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተጨማሪ ብድር ለመልቀቅ እያቅማሙ ነው።

ይህም የሆነበት ዋነኛው ምክንያት ተጨማሪ ብድር ለአገሪቱ መስጠት የመክፈል አቅሟን የበለጠ ሊያዳክም ይችላል ከሚል ስጋት ነው።

በገንዘብ ሚኒስትር አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን ለሮይተርስ እንደተናገሩት ለምሳሌ የቻይናው ኤክዚም ባንክ እሰጣለው ብሎ የነበረውን ከፍተኛ ገንዘብ ለመልቀቅ ፍቃደኛ ሳይሆን መቅረቱን አንስተዋል።

የቻይናው ኤክዚም ባንክ ለኢትዮጵያ ለመስጠት የታቀበው የብድር መጠን 339 ሚሊዮን ዶላር ነው። ይህን ያሉት የገንዘብ ሚኒስቴር የቻይና ትብብር ዳይሬክተር ደምሱ ለማ ናቸው።

ሰኔ ወር ላይ በገንዘብ ሚኒስቴር የታተመ አንድ ሰነድ እንዳመለከተው የውጭ አበዳሪዎች አስከ መጋቢት መጨረሻ ድረስ 11 ቢሊዮን ዶላር ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቅ ነበር።

የዓለም ባንክ አንድ አካል የሆነው የዓለም አቀፉ የልማት ትብብር ማኅበር (ኢንተርናሽናል ዴቨሎፕመንት አሶሲየሽን) ለምሳሌ 3.3 ቢሊዮን ዶላር ይለቃል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረ ሲሆን ይህን እስከአሁን ተግባራዊ አላደረገም።

ሚኒስቴሩ በሰነዱ ከጠቀሳቸው ሌሎች አበዳሪ ተቋሟት አንዱ ግዙፉ የዓለም የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ሲሆን ተቋሙ 2.7 ቢሊዮን ዶላር እስከ አሁን ለኢትዮጵያ አለቀቀም።

ከውጭ አበዳሪዎች ትልቅ የምትባለው ቻይና 1.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር አልለቀቀችም። ከላይ ከተጠቀሱት አበዳሪዎች ሌላ የአፍሪካ ልማት ባንክ እና ሌሎች የንግድ ባንኮችም ይገኙበታል።

ይህ የውጭ አበዳሪዎች ተጨማሪ ብድር ለኢትዮጵያ ለመልቀቅ አለመፍቀዳቸው አገሪቱ ላይ እየተካሄዱ ያሉ መጠነ ሰፊ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ሊያስተጓጉል እንደሚችል ይገመታል።

በውጭ ብድር ተጠቃሚ እየሆኑ ከቆዩት ፕሮጀክቶች መካከል እርሻ፣ ትራንስፖርት፣ ኮሚዩኒኬሽን፣ አውራ ጎዳናዎች እና የባቡር ፕሮጀክቶች ይገኙበታል።

እነዚህ በድምሩ 675 ቢሊዮን ዶላር ብድር ያገኙ ፕሮጀክቶች ናቸው።
ይህም እንደ አውሮፓውያኑ ከሐምሌ 2020 እስከ መጋቢት 2021 ያለውን የሚያመላክት አሐዝ ነው።

አሁን የውጭ አበዳሪዎች ለኢትዮጵያ ተጨማሪ ገንዘብ ለማበደር ታቅበው ሁኔታውን ቆም ብለው እያጤኑት የሚገኙት አገሪቱ የብድር እፎይታን በተመለከተ በዓለም አቀፍ ደረጃ ንግግር የጀመረች በመሆኑ ነው።

ባለፈው ሐምሌ ወር የአይኤምኤፍ ቃል አቀባይ ጌሪ ራይስ በኢትዮጵያ የብድር ጉዳይ ላይ አንድ ኮሚቴ በፍጥነት እንዲቋቋም ጥሪ አድርገው ነበር።

ይህም ከቡድን 20 እና ከፓሪስ ክለብ አበዳሪዎች ዘንድ ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የብድር እፎይታ ጥያቄ እንዲመለከት ነበር።

መንግሥት የብድር መመለሻ እፎይታ ለማግኘት ንግግር መጀመሩ ግን ስህተት አለመሆኑን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከውጭ የተበደረችው ዕዳ እስከ መጋቢት ወር ብቻ 29 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። ይህም የጥቅል አገር ውስጥ ምርት እድገት (ጂዲፒ) 27 ከመቶ የያዘ ነው።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን ቻናላችንን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።

ቢቢሲ
ነሃሴ 12 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *