ቅርሶች ከመፍረሳቸው በፊት እንዳንደርስ ያደረገን የመንግስት መስሪያ ቤቶች ምን ሊሰሩ እንደሆነ ቀድመን ባለማወቃችን ነው ሲል የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ገለፀ

የመንግስት መስሪያ ቤቶች ምን ሊሰሩ እንደሆነ ቀድመን አለማወቃችን ለቅርሶች እንዳንደርስ አድርጎናል ብሏል የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ በቅርሶች መፍረስ ብዙ ቅሬታዎች ተነስተዋል።

ከሰሞኑም የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽኑ የራስ ሀይሉ ተክለሀይማኖት መኖሪያ ቤት ፈርሷል በሚል የአዲስ አበባ ባህል ቱሪዝምና ኪነጥበብ ቢሮ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደወሰደው ይታወቃል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ በበጀት አመቱ መጀመሪያ ላይ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ማን ምን ሊሰራ እንደሆነ ባለማወቃችን ለቅርሶች ልንደርስ አልቻልንም፣ የምናውቀው ማፍረስ ሲጀመር ነው ሲሉ የባለስልጣኑ የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ጌታቸው ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል።

በተለያዩ የምክክር መድረኮች አብረውን ከሚሰሩ የመንግስት ቢሮዎች ጋር ለመገናኘት እንሞክራለን ያሉት ዳይሬክተሯ በእቅድ ዝርዝራቸው ላይ ቢያሳውቁን በጋራ ለመስራት እንችላለን ብለዋል።

በአዲስ አበባ ቅርሶች የያዙት ቦታ ያጓጓል ነገር ግን የከተማ ልማት ቅርሶችንም ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሊሰራ ይገባል ሲሉም አጽኖት ሰጥተዋል።

በከተማዋ ያሉ ቅርሶች በእድሜ ብዛትና በግዴለሽነት ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሆነ ተነግሯል።

የባለስልጣኑ የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ጌታቸው በአሁን ሰአት ያለው የአዲስ አበባ ነዋሪ የቅርስ አረዳድና አጠባበቅ የሚበረታታ ነው ያሉ ሲሆን አመራሩ ግን አውቆ ከማጥፋት ሊቆጠብ ይገባል ብለዋል።

አክለውም በዚሁ ከቀጠለ ከተማዋን ቅርስ አልባ ወደማድረግ እየሄድን ነው ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን ቻናላችንን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
መቅደላዊት ደረጄ
ነሐሴ 26 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *