“አሁንም ከመንግስት ጋር ለመስራት ዝግጁ ነን “ የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ

የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ አሁንም ከመንግስት ጋር ለመስራት ዝግጁ ነው፣ ነገር ግን ምን አይነት የሀላፊነት ቦታ ላይ እንደምንመደብ ቀድሞ ሊነገረን ይገባል ሲሉ የፓርቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር አብዱልቃድር አደም ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል።

በዛሬው ዕለት በተካሄደው 6ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ አመት የስራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አብዱልቃድርን ለአዲስ አበባ ምክር ቤት የካቢኔ አባልነት ተጠይቀው ፓርቲያቸው እንዳልፈቀደ መናገራቸው አይዘነጋም።

ፓርቲያችሁ ያልፈቀደበት ምክንያት ምንድነው? ያልናቸው ፕሬዝደንቱ በመጀመሪያ የተነገረን በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ በፓርቲያችን መመሪያ መሰረት እነሱ የመረጡትን ሰው ሳይሆን እኛ ለቦታው ይመጥናል ብለን ያመንበትን ሰው መመደብ እንዳለብን ስለሚደነግግ ነው ሲሉ መልሰዋል።

በተጨማሪም ከመንግስት ጋር መስራት አለብን ብለን በማመናችንም ባይቀበሉትም ሌላ ሰው እንደመደብን አሳውቀን ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ይህንን በምክር ቤቱ አላነሱትም ብለዋል የፓርቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር አብዱልቃድር።

አሁንም ቢሆን ፓርቲያችን ከመንግስት ጋር ሊሰራ ዝግጁ መሆኑን እናሳውቃለን ፣ ነገር ግን ጥሪ ሲደረግልን ግልጽነት እንዲኖርና ትክክለኛውን ሰው እንድንመድብ ግለሰብን ሳይሆን ፓርቲውን በመምረጥ መሆን አለበት ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

መቅደላዊት ደረጄ
መስከረም 26 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *