“የተሾምኩበት በትክክለኛው ቦታ ነው፣ከዚህ ሃላፊነት ውጪ ቢሰጠኝ ኖሮ አልቀበልም ነበር” ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፀደቀው የሚንስትሮች ሹመት የትምህርት ሚንስትር ሆነው የተሾሙት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የተሾምኩበት በትክክለኛው ቦታ ነው፣ከዚህ ሃላፊነት ውጪ ቢሰጠኝ ኖሮ አልቀበልም ነበር ብለዋል፡፡

ይህንን ሃላፊነት እንደማገልገል ከወሰድነው ከዚህ መስሪያ ቤት ውጪ ሌላ ሃላፊነት ቢሰጠኝ አልወስድም ነበር፡፡ ትምህርት በፍቅር የሚሰራ ስራ ነው፡፡የትምህርት ሚንስቴርም ትልቅ ተቋም ነው የተሰጠኝም ሃላፊነት ትልቅ ሹመት ነው በማለት ተናግረዋል፡፡

ሹመቱንም በዛሬው እለት እንደ ሌላው ሰው ነው የሰማሁት ያሉት ፕሮፌሰሩ፣እድሜ ዘመኔን በማስተማር ስራ ላይ ነው ያሳለፍኩት፣ምናልባት ፔዳጎጂ እንደመስፈርት ይቆጠር እንደሆነ አላውቅም ብለዋል፡፡

የአገሪቱን ቀጣይ እጣ ፈንታ ለመወሰን ሁለት ጉዳዮች ከግንዛቤ ውስጥ መግባት እንዳለባቸው ያነሱት ፕሮፌሰሩ እነዚህም የአገሪቱን ፖለቲካዊ ሁኔታ ማሻሻል እና ትውልዱን በትምህርት ማነፅ ነው ብለዋል። አክለውም ላለፉት 40 ዓመታት በችግር የተተበተበው የትምህርት ዘርፍ የሚጠበቅበትን መስራት አልቻለም ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ)፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮችን ነው የካቢኔያቸው አባላት አድርገው በዛሬው እለት ሾመዋል፡፡

በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) መሪ ፕ/ር ብርሀኑ ነጋ የትምህርት ሚኒስትር፤ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀመንበር በለጠ ሞላ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር እንዲሁም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ምክትል ሊቀመንበር ቀጄላ መርዳሳ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሆነው ተሾመዋል፤ ቃለ መሃላም ፈጽመዋል፡፡

ሔኖክ ወ/ገብርኤል
መስከረም 26 ቀን 2014 ዓም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *