በአዲስ አበባ ከተማ በተመረጡ ቦታዎች በየሣምንቱ እሁድ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች ባዛር ሊዘጋጅ እንደሆነ ተነገረ።

በአዲስ አበባ ከተማ እየታየ ያለውን የኑሮ ውድነት ለመቆጣጠር እንዲሁም በምርት አቅርቦትና ስርጭት የሚፈጠረውን ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረት ለመቀነስ እንዲያስችል ባዛር ማዘጋጀት ማስፈለጉን የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ አስታውቋል ፡፡

ባዛሩ በአቅራቢውና በሸማቹ መካከል የሚገኘውን የአቅርቦት ሰንሰለት ለማሳጠርና የገበያ አማራጮችን ለማስፋት ያለመ መሆኑን የንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ ገልጸዋል።

ለንግድ ባዛሩ የመጀመሪያ ዙር 20 ቦታዎች መዘጋጀታቸውን ተዘጋጁ ሲሆን የፊታችን እሁድም የትራንስፖርት መዳረሻ እና የሕዝብ ብዛትን መሠረት በማድረግ በመገናኛ፣ ፒያሳ፣ ሜክሲኮ አደባባይ፣ ቃሊቲ መናኸሪያ እና ጀሞ 67 ቁጥር ማዞሪያ የሙከራ ስራ ይጀመራል ብለዋል።

በባዛሩም ከግብርና እና ከኢንዱስትሪ ምርቶች መካከል የጤፍና የስንዴ ዱቄት፣ የባልትና ውጤቶች፣ ጥራጥሬና፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች በተጨማሪ ዘይት፣ ማካሮኒና ፓስታ ይቀርባሉ ብለዋል ኃላፊው፡፡

በዚህ ባዛር ትኩስ የግብርና ምርቶችን ለሸማቹ ማድረስ፣ በአምራችና በሸማቹ መካከል ያለውን የአቅርቦት ትስስር በማሳጠር አማራጭ የግብይት ስፍራን መፍጠር እንዲሁም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የህብረተሰብ ክፍሎች የኑሮ ጫና መቀነስ መሆኑን አቶ አደም ተናግረዋል፡፡

በባዛሩ አቅርቦት ላይም በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የሚገኙ የኅብረት ስራ ማህበራትና አርሶ አደሮች፣ የአዲስ አበባ ኅብረት ስራ ማኅበራት፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ የሰብልና አትክልት አቅራቢዎች ወይም የጅምላ ነጋዴዎች እና በምግብ ማቀነባበር የተሰማሩ ፋብሪካዎች እንደሚሳተፉ ኃላፊው ጠቁመዋል።

ጥቅምት 19 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *