በሀዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ አካል ጉዳተኛ መስለው ህብረተሰቡን ሲያጭበረበሩ የተገኙ 2 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ህብረተሰቡ በሚያደርጋቸው በማንኛውም እንቅስቃሴ በአካል ጉዳተኝነት እና በሌላም ሽፋን ወንጀል የሚፈጽሙ አካላት በየአካባቢው በመኖራቸው ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ፖሊስ አሳስቧል።

በትላንትናው ዕለት ማለትም ጥቅምት 24/2014 ዓ.ም በቁጥጥር ስር እንደዋሉ የተነገረው 2 ግለሰቦች ፍጹም ጤነኛ ሆነው ሳሉ አካላቸው ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸውና ተንቀሳቅሰው መስራት እንደማይችሉ በማስመሰል ህብረተሰቡን የማጭበርበር ወንጀል ሲፈጽሙ እንደተገኙ የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ገልጿል።

ግለሰቦቹ ይህን ተግባር ለመፈጸም ጎማ ከጀርባው እስከ እግር ታፋቸው በማሰር ሲንቀሳቀሱ እንደነበርና ህብረተሰቡ ለፖሊስ በሰጠው ጥቆማና ፖሊስ ባካሄደው ክትትል በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።

ፖሊስ ግለሰቦቹን በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ በጤንነታቸው ላይ ባካሄደው ምርመራ መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ማረጋገጡን የሀዲያ ዞን ፖሊስ ማህበረሰብ ወንጀል መከላከል ዲቪዥን ኃላፊ ኮማንደር ሳህሉ ኃይሌ ተናግረዋል።

በመቀጠልም ፖሊስ የግለሰቦቹን ማንነት እንዲሁም ፍላጎታቸው የገንዘብ መሆኑን አልያም ደግሞ ከጥፋት ሃይሎች ጋር ቁርኝት ያላቸው መሆኑን ለማጣራት ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝ ኮማንደሩ ጠቁመዋል።

እንደ ኮማንደር ሳህሉ ገለጻ ፖሊስ ይህን ፍንጭ በመጠቀም በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች በአካል ጉዳተኝነትና በሌላም ሽፋን የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ልየታ እያደረገ ነው።

ህብረተሰቡ በሚያደርጋቸው ማንኛውም እንቅስቃሴ በአካል ጉዳተኝነት እና በሌላም ሽፋን ወንጀል የሚፈጽም አካላት በመኖራቸው ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

በተጨማሪም ህብረተሰቡ መሰል የወንጀል ድርጊት ሲጋጥመውና ሌሎች መረጃዎችን ለመስጠት 046-555-03-30 በመደወል ለፖሊስ ጥቆማ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
ጥቅምት 26 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *