የአልጄሪያ ፕሬዝዳንት ስለ ህዳሴ ግድብ ከግብፅ አቻቸው ጋር ለመምከር ካይሮ ገብተዋል

የግብፅ መሪ ፅ/ቤትን ጠቅሶ ኤ ኤፍ ፒ እንደዘገበው የአልጄርያ ፕሬዝዳንት አብደልማጂድ ቴቡኔ ትናንት ካይሮ የገቡ ሲሆን የግብፅ አቻቸው ፕሬዝዳንት አብድል ፈታህ አልሲሲ በካይሮ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው ተቀብለዋቸዋል፡፡

የአልጄርያው ፕሬዝዳንት አብደልማጂድ ቴቡኔ በግዙፉ ፕሮጀክት ምክንያት በኢትዮጵያ፣በግብፅ እና በሱዳን መካከል ያለውን አለመግባባት አስመልክቶ ከአልሲሲ ጋር ለመወያያት ወደ ካይሮ ካቀኑባቸው ዋነኛ ጉዳዮች መካከል ነው፡፡

በተጨማሪም ትናንት የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ በሙስካት ከኦማን አቻቸው ሰይድ ባድር አልቡሰይዲ ጋር በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ‹‹በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር የሚደረገውን ውይይት ለመቀጠል ‹ፖለቲካዊ ፍላጎት› ካለ በእኛ በኩል ዝግጁዎች ነን›› ብለዋል፡፡

የአልጄርያው ፕሬዝዳንትም ህዳሴ ግድብን አላማው ያደረገ ጉዞ ወደ ግብፅ አድርገዋል፡፡

ለአመታት ለዘለቀው ግጭት መፍትሔ በመፈለግ ሂደት ውስጥ አልጄርያ ለማደራደር ስትሞክር ነበር፡፡ ለዚህ የአህጉሪቱ አንገብጋቢ ጉዳይ አልባት ለማምጣት የበኩሏን ሙከራ እንደምትቀጥልም አልጄርያ እየገለፀች ነው፡፡

የአልጄርያው ፕሬዝዳንት አብደልማጂድ ቴቡኔ ስልጣን ላይ ከወጡበት 2019 ጀምሮ ይሄ ወደ ግብፅ ያደረጉት የመጀመርያው ጉዞ ነው፤ አልሲሲ እንደ አውሮፓውያኑ በ 2014 ወደ አልጄርያ አቅንተው ነበር፡፡

ፕሬዝዳንት ቴቡኔ በሁለት ቀን የካይሮ ቆይታቸው ከህዳሴ ግድቡ በተጨማሪ በሊቢያ ስላለው ግጭት ይነጋገራሉ ተብሏል፡፡

የመጀመርያውን የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ባለፈው ወር ለማድረግ ሙከራ ላይ የነበረችው ሊቢያ ሳይሳካላት ቀርቷል፡፡

የግብፅና የአልጄርያ መሪዎችም ሊቢያ ምርጫውን ስለምታደርግበትና ሉአላዊነቷና የግዛት አንድነቷ ስለሚጠበቅበት ሁኔታ እንደሚመክሩ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

ሔኖክ አስራት
ጥር 17 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *