በአማራና አፋር ክልል በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት እና በንብረት ላይ ከ1.1 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት መድረሱ ተመለከተ

የህወሃት ወራሪ ቡድን በአማራና በአፋር ክልሎች በፈፀመው ወረራ ምክንያት በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት በመቋረጡ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ከመሆኑ በተጨማሪም በተቋሙ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አሰከትሏል፡፡

ወራሪ ቡድኑ በክልሎቹ በፈጸመው ዝርፊያና ንብረትን የማውደም ተግባር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በድምሩ ብር 1 ቢሊዮን 122 ሚሊዮን 304 ሺህ 395 ብር 37 ሳንቲም የሚደርስ ውድመት እና ኪሳራ እንደደረሰበት ተቋሙ ያካሄደው የጥናት ውጤት አመልክቷል።

ተቋሙ የጉዳቱን ሁኔታ እንዲያጠና ባደራጀው አጥኚ ቡድን ግኝት ሪፖርት መሰረት በአፋር ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰር ባሉ በ6 አገልግሎት መሰጫ ማዕከላት እንዲሁም በአማራ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ5 ዲስትሪክቶች ስር የሚገኙ 30 አገልግሎት መስጫ ማዕከላት፣ 2 ዲስትሪክት ጽ/ቤቶች እና የፕሮጀክት ማስተባበሪያዎች ሙሉ በሙሉ እና በከፊል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ተቋሙ ከኤሌክትሪክ ቢል ሽያጭ ሊሰበስብ ካቀደው ከ336 ሚሊዩን ብር ገቢ በላይ እንዲያጣ ያደረገው ሲሆን፤ በእነዚህ አካባቢዎች አገልግሎት ያገኙ የነበሩ ከተቋሙ ጋር ቀጥተኛ ውል ያላቸው 278 ሺህ 395 ደንበኞች አገልግሎት ተቋርጦባቸው ቆይቷል፡፡

ይህም በቤተሰብ ደረጃ ሲታይ 1 ሚሊዮን 531 ሺህ 173 ያህል ዜጎች በቀጥታ ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ውጪ ሆነዋል።

ይህን ሁሉ ተደምሮ ተቋሙ የህዋሃት ወራሪ ቡድን በአማራና በአፋር ክልሎች በፈፀመው ወረራ ምክንያት በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት እና በንብረት ላይ ከ1.1 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት እንደደረሰበት የተደረገው ጥናት መደረሱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አሳውቋል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
ጥር 24 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *