ብስክሌትን ለትራንስፓርት አገልግሎት ለማዋል ያስችላል የተባለ እቅድ ቀረበ፡፡

በመዲናዋ ደህንነቱ የተጠበቀ የብስክሌት ትራንስፖርትን ለመተግበር አማራጭ ይሆናል የተባለ የዕቅድና የዲዛይን መሪ ሀሳብ ይፋ ሆኗል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ አስተባባሪነት በብሉምበርግ ኢኒሼቲቪ ድጋፍ፤ የቀረበው ይህ መሪ ሃሳብ የብስክሌት ኔትወርክን ማሳደግና አገልግሎቱን ማዘመን በትራንስፓርት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተነስቷል፡፡

በዋናነት እቅዱ የብስክሌት ማቆሚያ ቦታዎችና መሰረተ ልማቶች እንዲኖሩ ከማድረግ ባለፈ በቂ የብስክሌት መለማመጃ ቦታዎች እንዲኖሩ እገዛ ያደርጋል ተብሏል፡፡

የአዲስ አበባ ትራንስፓርት ቢሮ ተወካይ ኢንጂነር ቀጄላ መኮንን የትራንስፖርት አገልግሎቱን እገዛ የሚያደርግ የሞተር አልባ ትራንስፖርት በመዲናዋ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝና በማንሳት የብስክሌት መሰረተ ልማት ዲዛይን የመሪ ሀሳብ ይፋ መደረጉ ደግሞ አማራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጥ ከማስቻሉም ባሻገር በማህበረሰቡ ዘንድ እንደባህል ሆኖ ጠቀሜታው ከፍ እንዲል ያስችላልም ብለዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት በብሉምበርግ ኢኒሼቲቭ የአዲስ አበባ አጋር የሆነው የወርልድ ሪሶርስ ኢንስቲትዩት ትራንስፖርት ፕላነር ኢንጂነር ጂሬኛ ሂርጳ በበኩላቸው ብስክሌትን የትራንስፖርት አማራጭ አድርጎ መጠቀም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ገልፀዋል፡፡

በዚህ ረገድ ጤናማ ዜጋ ከመፍጠር አኳያ ከፍተኛ ሚና እንዳለው የጠቆሙት ኢንጂነሩ በአካልና በስነ-አእምሮው ብቁ፤ ረዥም እድሜና ጤናማ ህይወት እንዲኖር ይረዳል ብለዋል፡፡

የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ ብስክሌትን መጠቀም ተመራጭ ትራንስፖርት ተደርጎ መወሰድ እንዳለበትም ኢንጂነር ጂሬኛ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር ለተሸከርካሪዎች ለነዳጅ በዓመት ከፍተኛ በዶላር የሚተመን ወጪ እንደሚወጣ በመጠቆም ብስክሌትን የትራንስፖርት አማራጭ አድርጎ መጠቀም ይህንን በመቀነስ ረገድ የማይናቅ ሚና እንዳለው ኢትዮ ኤፍ ኤም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ያገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
ጥር 24 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *