የናይጄሪያው ፕሬዝደንት ሙሃመዱ ቡሃሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ኢትዮጵያን በአንድነት እንዲይዙ አሳሰቡ

ፕሬዝደንት ሙሃመዱ ቡሃሪ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ችግሮችን ተቋቁመው ሀገሪቱን በአንድነት በማቆየት ላይ እንዲያተኩሩ አሳስበዋል።

በአፍሪካ ህብረት ዋና መሥሪያ ቤት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ባደረጉት ውይይት ነው ይህንን አደራ ያስተላለፉት፡፡

ናይጄሪያ በሰላም አብሮ በመኖር እና አንድነትን በማጠናከር ላይ የሚደረገውን ጥረት መደገፏን ትቀጥላለች ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገሪቱን ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ፣ በልማት ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ያደረጉትን ጥረት አድንቀዋል።

ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት “ልክ እንደ ናይጄሪያ ትልቅ እና የተለያዩ ማንነቶች ያሉባት ሀገር እየመሩ ነው እናም የሚፈለገውን ተፅእኖ ለመፍጠር የሚከፈለውን መስዋዕትነት አውቃለሁ” ብለዋል ።

ቡሃሪ በቃል አቀባያቸው ፌሚ አዴሲና በኩል በሰጡት መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለሀገሪቱ ጠንካራ አመራር በመስጠት ልማትን በማረጋገጥ ረገድ ያለውን መልካም ስራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አበረታተዋል ሲል ዲይ ሊ ትረስት ዘግቧል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቡሃሪ ባለፉት አመታት በሀገራዊ እና በአህጉራዊ ጉዳዮች ላይ በተለይም አንድነትን እና መረጋጋትን ለማበረታታት ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል።

የአፍሪካ አህጉር በግጭቶች ሳቢያ ያስመዘገበው እድገት አዝጋሚ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እንደ ናይጄሪያ እና ኢትዮጵያ ያሉ ትልልቅ ኢኮኖሚ ባለቤቶች በአህጉሪቱ እድገትና ብልፅግናን የሚያጎለብት አመራር ሊሰጡ ይገባል ብለዋል።

በአህጉሪቱ ያገረሸው መፈንቅለ መንግስት ሀገራቱን የበለጠ የሚያዳክም እና የዲሞክራሲ እድገቶችን ሊቀለብስ እንደሚችል ጠቁመው ቡሃሪ በአስተዳደር ውስጥ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን ፈፅሞ አይታገስም በሚለው ላይ ያላቸውን አቋም አድንቀዋል።

ያይኔአበባ ሻምበል
ጥር 30 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *