የደህንነት ችግር እንዳያስከትሉ ለተሰጉ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ፍቃድ መሰጠት ተጀመረ፡፡

ለ 25 ሺ በግለሰብ እና በመንግስት እጅ ለሚገኙ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ፍቃድ መሰጠት መጀመሩን የቴክኖሎጂ እና መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ገለፀ፡፡

የቴክኖሎጂ እና መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በተቋቋመበት አዋጅ በተሰጠዉ ሃላፊነት መሰረት የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን መመዝገብ አንዱ እና ዋነኛዉ ሃላፊነቱ ነዉ ያሉት በኤጀንሲዉ የቴክኖሎጂ መረጃ እና መገናኛ ቁጥጥር እና ዉል ዝግጅት ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ተመስገን አስማረ ናቸው፡፡

ተቋሙ ይህንን ሃላፊነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ለቴክኖሎጂ መሳሪያዎቹ ፍቃድ መስጠት መጀመሩን አቶ ተመስገን ገልጸዋል፡፡

እነዚህ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች በሃገራችን ላይ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ እና ማህበራዊ ችግሮችን እንዳያስከትሉ ከደህንነት አንጻር ምዝገባዎች ተካሂደዉ ፍቃዱ መጀመሩ ነዉ የተገለጸዉ፡፡

ፍቃዱ የሚሰጣቸዉ መሳሪያዎች 6 ሲሆኑ ድሮን ፣ ጂፒኤስ፣ የሬድዮ መገናኛዎች፣ የወታደር መነጽሮች፣ ሳትፎኖች እና ቪሳቶች መሆናቸዉ ተገልጿል፡፡

እነዚህ መሳሪያዎች በጥቅሉ 25 ሺ ሲሆኑ በህዳር ወር ለተከታታይ 20 ቀናት ምዝገባቸዉ ተካሂዶ የነበረ ሲሆን ከሰኞ ጀምሮ ፍቃዱ እየተሰጣቸዉ ያሉትም እነዚህ ማስመዝገብ የቻሉት ብቻ ናቸዉ፡፡

ምዝገባዉ የተካሄደዉ በመላዉ ሃገራችን ሲሆን በአካል ቢሮዉ ድረስ መምጣት አስፈላጊ እንደነበርም ነዉ የተነሳዉ፡፡ ኤጀንሲዉ ፍቃዱ ለመስጠት መስፈርቶች አስቀምጧል፡፡

ለመስፈርቶቹ መካከል ከግልም ሆነ ከተቋም ሲመጣ ስለመሳሪያዉ ባለቤትነት የሚገልጽ ህጋዊ ደብዳቤ እና ህጋዊ መታወቂያ ይዞ መገኘት መሆኑ አንዱ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

እንደየስራ ባህሪያቸዉ መሰረት መቆጣጠር ፣ አደጋ እንዳያስከትል መጠንቀቅ እና ሃላፊነት መዉሰድ የሚችሉ ከኤጀንሲዉ ጋር ስምምነት በመግባት ንብረቶቻቸዉን እያስመዘገቡ ይገኛሉ፡፡

ፍቃድ መስጠቱ ለተከታታይ 3 ሳምንታት ይቀጥላል ተብሏል፡፡

ከዚህ በፊት በተሰጠዉ ግዜ ማስመዝገብ ያልቻሉ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች በቂ እና አሳማኝ ምክንያት ይዘዉ ሲቀርቡ እና ከመንግስት ፍቃድ ሲያገኙ ምዝገባ እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሏል፡፡

እስከዳር ግርማ
የካቲት 02 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.