የዩክሬን መከላከያ 50 የሩሲያ ወታሮችን መግደሉን አስታውቋል፡፡

እስካሁን ድርስ ስምንት የዩክሬን ዜጎች በሩሲያ ጥቃት መገደላቸው ሲነገር በርካቶች ቆስለዋል ተብሏል፡፡

የሩሲያ የጥቃት ኢላማ የተደረገችው ኪዬቭ የሲቪል አስተዳደርን ለጊዜው በወታደራዊ ህግ መተካቷን አሳውቃለች፡፡

ከደቂቃዎች በፊት ሮይተርስ የዜና ወኪል በዩክሬን መዲና ኪዬቭ ከሚገኘው የአገሪቱ ጦር ደኅንነት ዋና መሥሪያ ቤት ጥቁር ጭስ ሲወጣ ታይቷል ሲል ዘግቧል።

የዩክሬን ወታደራዊ እና የደኅንነት ተቋማት በሩሲያ የሚሳኤል ጥቃቶች ዒላማ መደረጋቸውን የዩክሬን ባለሥልጣናት እና የዓይን እማኞች ቀደም ሲል ሲናገሩ ነበር፡፡

ሩሲያ የዩክሬን ወታደራዊ የጦር ሰፈሮች ላይ እንዳነጣጠረች የገለጹት ደግሞ የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ በአገሪቱ ወታደራዊ ሕግ ደንግገዋል።

መቼ እንደሆነ በግልጽ ባይነገራቸውም ሩሲያ ጥቃት ልትሰነዝር እንደምትችል ከዚህ ቀደም ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው የዩክሬን ዜጎች በመኖሪያ ቤታቸው እንዲቆዩ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል።

የዩክሬን መከላከያ ለሀገሪቱ ዜጎች “ተረጋጉና በዩክሬን ወታደራዊ ኃይል ተማመኑ” ሲል ባወጣው መግለጫ ገልጿል።

እስካሁን ዩክሬን አምስት የሩሲያ አውሮፕላኖች እና ሄሊኮፕተሮች መታ እንደጣለች ስትናገር፤ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ ነገሩን አስተባብሏል እንደ አልጀዚራ ዘገባ፡፡

የጀርመኑ መራሂተ መንግስት ኦላፍ ሾልስ “ሩሲያ በዩክሬን ላይ የሰነዘረችው ጥቃት በግልጽ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን የሚጥስ ነው ሲሉ። የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ፑቲን “የደም መፋሰስን መንገድ መርጠዋል” ብለዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በሩሲያ ላይ አዲስ ማዕቀብ እንደሚጥሉ ቃል ገብተዋል።

የሩሲያው ፕሬዝደንት በአገራቸው የቴሌቭዥን ጣቢያ ባደረጉት ንግግር ጥቃቱ በምሥራቃዊ ዩክሬን የሚገኙ ሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት ለመጠበቅ አስፈላጊ ነው የሚል ማመካኛ አቅርበዋል።

አሜሪካ የሩሲያው ፕሬዝደንት ዩክሬንን ለመውረር እንዲህ አይነት ምክንያት እንደሚያቀርቡ አስቀድማ አስጠንቅቃ ነበር።

ያይኔአበባ ሻምበል
የካቲት 17 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.