የአቡነ መርቆርዮስ የቀብር የሽኝት መርሀግብር ቅዳሜ ይደረጋል ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዎስ የቀብር የሽኝት መርሀግብር በመጪው ቅዳሜ በመስቀል አደባባይ ይደረጋል፡፡

ባሳለፍነው የካቲት 25/2014 ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት የተለዩት አቡነ መርቆርዮስ የቀብር ስርአታቸው እሁድ የሚደረግ ሲሆን በመጪው ቅዳሜ ከጠዋቱ 3 ሰአት ጀምሮ እስከ 7 ሰአት ከ45 ድረስ የሽኝት መርሀግበር መዘጋጀቱን ቤተክርስቲያኗ አስታውቃለች፡፡

ቅዳሜ እለት በሚኖረው የሽኝት መርሀግብር ላይ ከሀገሪቱ በሁሉም አካባቢ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የሚሰባሰቡ ሲሆን ሀገራትን ወክለው የሚመጡ ዜጎችም ይሳተፋሉ ብላለች ቤተክርስቲያኗ፡፡

እሁድ ከማለዳው ጀምሮ በሚደረግ የፍታት ስነ ስርአት በኃላ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ስርአተ ቀብራቸው የሚፈጸም ይሆናል ተብሏል፡፡

ትውልዳቸው በቀድሞው የጎንደር ክፍለ ሀገር በደብረ ታቦር አውራጃ አረጊት ኪዳነ ምሕረት ልዩ ስሟ ማር ምድር ነው፡፡

ብፁዕነታቸው ከአባታቸው ከብላታ ፈንታ ተሰማ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ለምለም ገሰሰ በ1930 ዓ.ም አብዝታ የፈተነቻቸውን ግን ንቀው በአርምሞ ድል ያደረጓትን ምድር ተቀላቀሉ፡፡

ቅዱስነታቸው ባሳለፍነው የካቲት 25 ቀን 2014 ዓ.ም በተወለዱ በ84 አመታቸው በድካም መለየታቸው ይታወሳል፡፡

ሔኖክ ወ\ገብርኤል
የካቲት 29 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *