“ኢትዮጵያዊነት” በትምህርት ካሪኩለም ዉስጥ ተካቶ እንዲሰጥ ለማድረግ እስራለሁ— ኢትዮጵያዊነት የዜጎች መብት ማስተባበሪያ ድርጅት

ኢትዮጵያዊነት የዜጎች መብት ማስተባበሪያ ድርጅት ወይም በአጭሩ “ኢትዮጵያዊነት” ከሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅት ኤጀንሲ ፈቃድ አዉጥቶ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ሲሆን በዋናነት አንድነትን የሚያጎሉ ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ገልጿል፡፡

ከኢትዮጵያዊነት በላይ ብሄር ላይ ትኩረት ተደርጎ ሲቀነቀን የቆየዉ የብሄር ፌደራሊዝም ዋጋ እያስከፈለን እንደሚገኝ ገልጾ፣ አሁንም አንድነታችንን የሚያጠብቁ እሴቶች ላይ ካልተሰራ ስጋቱ ቀጣይነት ያለዉ መሆኑን አስታዉቋል፡፡

የኢትዮጵያዊነት ስራ አስኪያጅ አቶ ሞገስ በቀለ እንዳሉት፡- ድርጅቱ ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎሉ እና አንድነትን የሚያጠናክሩ እሴቶችን የሚያበረቱ ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ ይንቀሳቀሳል፡፡

በዚህም ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ድረስ፣ የኢትዮጵያዊነት ክበባትን ከማቋቋም ጀምሮ በትምህርት ካሪኩለም ዉስጥ እንዲካተት እስከማድረግ የደረሰ ስራን እንደሚያከናዉን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የሁሉም ማንነቶች የሚራመዱበት፣ስለ ኢትዮጵያ አንድነት እና የጋራ እሴቶች ላይ ምሁራን ጥናትና ምርምር የሚያካሂዱበት የኢትዮጵያዊነት ኢንስቲትዩትን ለመገንባት እቅድ እንዳለዉም ዋና ስራ አስኪያጁ አብራርተዋል፡፡

ልዩነት ላይ የሰራነዉን ያህል አንድነት ላይ አልሰራንም፤ህዝቡም በልዩነት የተሰበከዉን ያህል አንድነቱ አልተሸረሸረም፤በመጠኑም ቢሆን የተፈጠረዉን ስንጥቅ አክሞ ጠንካራ አንድነትን ለማረጋገጥ ኢትዮጵያዊነት ላይ መስራት ይገባናል የሚሉት ደግሞ የኢትዮጵያዊነት የቦርድ አባልና የሰሜን አሜሪካ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ተስፋሚካኤል መኮንን ናቸዉ፡፡

ለባህል፣ለቋንቋ እና ለእኩልነት ትግል ማድረግ ተገቢነቱ ባያጠያይቅም፣ አገራዊ ማንነት ግን ሁልጊዜም ቅድሚያ ሊሰጠዉ ይገባል ባይ ናቸዉ፡፡

ህገ-መንግስቷን በብሄር ተኮር ፌደራሊዝም ላቆመች ሀገር፣ ብሄርን ከአገራዊ ማንነት በላይ ማጉላትና አብዝቶ ማቀንቀን የጥፋት መሳሪያ እንዳይሆን ጥንቃቄ ያሸዋል ሲሉም ያነሳሉ፡፡

ለዚህም ኢትዮጵያዊነት የዜጎች መብት ማስተባበሪያ ድርጅት፣ከልዩነት ይልቅ አንድነትን የሚያጎሉና የጋራ እስቶችን የሚያጠናክሩ ስራዎች ላይ ተግቶ እንደሚሰራ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

በሙሉቀን አሰፋ

መጋቢት 13 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *