“ስንተሳሰብና ስንቀራረብ ከባድ የመሰለው ሁሉ እንደሚቀል ፣በደማቸው ሀገራችንን ካቆዩልን አባቶቻችን እንማራለን” የጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማህበር

የሚያዚያ 27 የድል በዐልን በደማቅ ሁኔታ ለማክበር እየተዘጋጀ የሚገኘው የጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማህበር በደማቸው ሀገራችንን አንድ አድርገው ካቆዩልን አባቶቻችን መተሳሰብን በመማር የፆም ወቅቱንና በዐሉን ልናሳልፈው ይገባል ብሏል፡፡

የጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት በደማቸው ሀገራችንን ካቆዩልን አባት አርበኞቻችን ጥበብ መማር ከቻልን የማያልፉ የሚመስሉ ችግሮቻችንን ማለፍ እንችላለን ብለዋል፡፡

በቅድሚያ ማህበሩ ከየትኛዉም የፖለቲካ ጉዳዮች የራቀ የሲቪል ማህበር መሆኑን ማስታወስ ይገባል ብለዋል የጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ፡፡
በሃገራችን የረሀብ፣ ያለመግባባት ችግር፣ በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ ጦርነት አለ ታዲያ ይሄ በሁሉም ሀገር ያለ ጉዳይ አዲስ ነገር እንዳልሆነ እየታወቀ ኢትዮጵያ ላይ ሲሆን እንደ ትልቅ ጉዳይ እያየን ስለምናራግበዉ ነው የሚከብደውና የሚወሳሰበው ሲሉ ተናግረዋል ፡፡
በፖለቲካ መስመር የተሰማሩት ወይም ተጎዳን የሚሉት አካላት ተሰባስበዉ የሚፈቱት ነገር ነዉ ብዬ አምናለሁ ያሉ ሲሆን ከዚህ በፊትም ችግሮች በእንደዚህ አይነት መንገድ መፈታታቸውን አስታውሰዋል፡፡
የአድዋን ጦርነት ፣ የዚያድባሬን ወረራ እንደ ምሳሌ ያነሱት ፕሬዝዳንቱ ችግሩ የሚፈታ ነዉ ፣ እንኳን የእርስ በዕርስ ግጭትና ጦርነት ይቅርና ከዉጭ መንግስታትም ጋር ቢሆን የነበሩብንን ችግሮች መፍታት ችለናል ብለዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት በመጀመሪያ ደረጃ ሰላም እንዲኖር ያስፈልጋል የሚሉት ፕሬዝዳንቱ ፤ለምንድነዉ እንዲህ የሆነዉ፣ እንዴት እናድርገዉ ብሎ ቁጭ ብሎ መነጋገር ፣ መተሳሰብ፣ መፍትሄዉስ ምን ይሁን የሚለዉን ቁጭ ብሎ መመካከር ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ሁሉ ግን ሰላም ያስፈልጋልና፤ ሰላም እንዴት እናምጣ ?ለሚለው ትኩረት እንስጥ ሲሉ መክረዋል፡፡
ከዛ ዉጭ ግን አፈንግጦ ሊመጣ የሚችል ነገር ካለ የኢትዮጵያን አንድነት የማይፈልግ ነው ያሉ ሲሆን እንደኔ እምነት ብዙዎቹ ከዉጭ በሚገቡ አካላት እንጂ በሀገር ዉስጥ ባሉ ወንድማማቾች መሀከል የሚፈጠር አይደለም ብለዋል

ይህንንም ችግር የሚመለከታቸው አካላት ተነጋግረዉ እንደሚፈቱት አምናለሁ ሲሉ ገልጸዋል ፡፡
የሚያዚያ 27 የድል በዐልን በደማቅ ሁኔታ ለማክበር ሁሉም እንዲዘጋጅም ማህበሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡

እስከዳር ግርማ

ሚያዚያ 12 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *