የእድሜያቸዉን 81ኛ ዓመት ሻማ በቅርቡ ያበሩትና ትናንት ምሽት ህይወታቸዉ ያለፈዉ ኮሎኔል ፍስሃ ደስታ ምን አይነት ሰዉ ነበሩ?

በቅርብ ከሚያዉቋቸዉ ሰዎች የተሰጠ ምስክርነት፡-

የደርግ መንግስት ም/ፕሬዝዳንት የነበሩት ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ በ81 ዓመታቸዉ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል::

ሌትናል ኮሎኔል ፍስሃ ደስታ በ1933 ዓ.ም በሰሜናዊ የሃገሪቱ ክፍል ትግራይ አደዋ ተወለዱ፡፡
በወቅቱ ባላባት በሚል በአካባቢዉ ትልቅ ክብር ካላቸዉ አንዱ የነበሩት ብላታ ደስታ ወልደማሪያም ልጅ ናቸዉ፡፡

እድሜያቸዉ ለትምህርት ሲደርስም ንግስተ ሳባ ት/ቤት ጀምረዉ በኋላም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣በሀረር ሚሊታሪ አካዳሚ ተምረዋል፡፡
ከዛም ወደ አሜሪካ በማቅናት ወታደራዊ ስልጠናዎችን ወስደዋል፡፡

ኮሎኔል ፍስሃ ደስታን በቅርበት ከሚያዉቋቸዉ ሰዎች መካከል አንዷ የሆነችዉ ደራሲ እና ጋዜጠኛ ገነት አየለ ፣”ኮሎኔል ፍስሃ ደስታ በጣም የተረጋጉ፣ጨዋታ አዋቂ፣ሁሉን አክባሪ፣የተማሩና በተለይም በህግ ዙሪያ የጠለቀ እዉቀት ያላቸዉ ሰዉ ነበሩ” ስትል ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግራለች፡፡

የደርግ መንግስትን በመመስረት ስማቸዉ ከቀዳሚዎች መካከል የሚጠቀሰዉ ኮሎኔል ፍስሃ እስከ ምክትል ፕሬዝዳንትነት የሃላፊነት ደረጃ የደረሱ ናቸዉ፡፡

የሀረር ሚሊታሪ አካዳሚ ተመራቂ ፣ የክቡር ዘበኛ ፣ የሰራተኞች ፓርቲን ካቋቋሙ ሰዎች መሀከል አንዱ የሆኑት የቀድሞዉ የደርግ መንግስት ምክትል ፕሬዝዳንት ኮለኔል ፍስሀ ደስታ፣ነገሮችን በጨዋታ እያዋዙ መግለጽ የሚችሉ እንደነበሩ ደራሲና ጋዜጠኛዋ ገነት አየለ ነግራናለች፡፡

“የሰሜኑ ጦርነት እየተካሄደ በነበረበት ወቅት በጣም ስጋት ስለነበረኝ ደወልኩላቸዉ፣እርሳቸዉ እንዲህ ነበር ያሉኝ ‘ኢትዮጵያ በዚህ መልኩ የምትፈርስ ሃገር አይደለችም በዚህ አታስቢ’ ነበር ያሉኝ” ስትል ታስታዉሳለች፡፡

አቶ ዴቻሳ አንጌቻ ደግሞ ይህን አሉን፡፡
የቆድሞ ሰራዊትን በተመለከተ የተዘጋጀ አንድ ፕሮግራም ላይ ነበር ትዉዉቃችን፤ከዛም የቅርብ ጓደኛሞች እስከመሆን ደረስን፤በወቅቱ ስለነበሩ ታሪኮች ስጠይቃቸዉ ከበቂ ማብራሪያዎች ጋር ምላሽ ይሰጡኛል፣አንዳንዴ ምክር ጣል ያደርጉልኝ ነበር ሲል ነግሮናል፡፡

ስለ ኮሎኔል ሲያብራራም “በጣም ስስ ልብ ያላቸዉ፣ነገሮችን ሁሉ በቀልድ እያዋዙ የሚናገሩ ሰዉ ነበሩ” ይላል፡፡

ኮሎኔል ፍስሃ በጣሊያን ኤምባሲ ለ30 ዓመታት ያህል በቁም እስር የነበሩ ጓዶቻቸዉ ማለትም ሌፍቴናንት ጀነራል አዲስ ተድላና ኮሎኔል ብርሃኑ ባየህ እንዲፈቱ ለጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድም ደብዳቤ ጽፈዉ እንደነበር አቶ ዴቻሳ ያነሳሉ፡፡

በወቅቱ ከተሰሩ ስራዎች ሁሉ በ1967 ህዳር 14 የተደረገዉ ጅምላ ግድያ እጅግ እንደሚጸጽታቸዉና መደረግ አልነበረበትም በሚል ሁሌም እንደሚቆጩ ይነግሩኝ ነበር ሲል አቶ ደቻሳ ገልጾልናል፡፡

አሁን ባለዉ የሃገሪቱ ሁኔታም ከህግ ዉጭና ያለ ፍርድ ሰዎች ህይወታቸዉን ሲያጡ በእጅጉ ያዝኑ እንደነበርም ነግረዉናል፡፡

ኮሎኔል ፍስሃ ደስታ በ1962 ዓ.ም ከወ/ሮ ሐረገወይን ገ/ስላሴ ጋር ትዳር መስርተዉ እስከ ህልፈተ-ህይወታቸዉ ድረስ አብረዉ ይኖሩ ነበር፡፡
በትዳራቸዉም አንድ ወንድ ልጅ አፍርተዋል፤የልጅ ልጆችንም አይተዋል፡፡

ሚያዝያ 13 ቀን 2014 ዓም የ 81ኛ ዓመታቸዉን ሻማ ያበሩት ኮሎኔል ፍስሃ ደስታ፣ በነበረባቸዉ የልብ ህመም ምክንያት ትናንት እኩለ ሌሊት አካባቢ ህይወታቸዉ ማለፉንና የቀብር ስነ-ስርዓታቸዉም በነገዉ እለት በአዲስ አበባ ቅድስት ስላሴ ቤተ-ክርስቲያን 9፡00 ላይ እንደሚፈጸም ሰምተናል፡፡

በሙሉቀን አሰፋ

ሚያዝያ 29 ቀን 2014 ዓም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *