በቤንች ሸኮ ዞን ኩጃ ቀበሌ ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት መኖሩ ተነገረ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወደህ በኩጃ ቀበሌና ከተማ አካባቢ ግድያ ፣ የእንስሳትና የጦር መሳሪያ ዝርፊያ እየተፈጸመ መሆኑን የዞኑ ነዋሪዎች ተናግረዋል ፡፡

ነዋሪዎቹ እንዳሉት ለወረዳው የጸጥታ መዋቅር በወቅቱ ብናሳውቅም በፍጥነት ያለመድረስ ሁኔታዎች ይታያሉ ብለዋል፡፡

የዞኑ መንግስትም በዞንና በወረዳ የሚገኙ አመራሮች ላይ ጥብቅ ፍተሻና ክትትል ሊያደረግ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

ይህም በነዋሪውና አመራሩ መካከል ከፍተኛ ጥርጣሬና አለመተማመንን ፈጥሮ ቆይቷል ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም የዞኑም ሆነ የወረዳው አመራር የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ያለምንም ልዩነት ማስጠበቅ ተቀዳሚ ተግባራቸው አድርገው ሊሰሩ ይገባል ሲሉ ነው የተናገሩት።

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቀበሌ መንገሻ ለኢትዮ ኤፍኤም እንደተናገሩት በአካባቢው ለተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የአመራሩ እጅና ተሳትፎ አለበት ሲሉ ተናግረዋል ፡፡

እንደ ዞን ከአመራሩ ጋር በተደረገ ግምገማዎችና የጸጥታ መዋቅሩ ተቀናጅቶ መስራት ከጀመረ በኋላ በዞኑ አንጻራዊ ሰላም መምጣቱን ገልጸው ሰላሙን ዘላቂ ለማድረግ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ነው አስተዳዳሪው የተናገሩት፡፡

አሁን ላይ ጫካ ከገቡ ሽፍቶች በላይ በከተማ የጦር መሳሪያ አቀባዮች ፣ ቀለብ ሰፋሪዎችና ሎጂስቲክ አመቻቾች ችግር እየፈጠሩ መሆኑን ገልጸው ህብረተሰቡ እነዚህን አካላት ለመንግሰት አሳልፎ ሊሰጥ ይገባል ብለዋል፡፡

በጦር መሳሪያ መብዛት ሰላም አይረጋገጥም ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ሰላም ወንድማማችነትና እህትማማችነትን በማጠናከር ፣ ጥርጣሬና አለመተማመንን በማስወገድና ወንጀለኞችን አሳልፈን ስንሰጥ ብቻ ነው ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የቤንች ሸኮ ዞን ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ዶክተር ካሳ እንደተናገሩት የኩጃ ቀበሌ ነዋሪዎች በቅድሚያ በጉያቸው የያዟቸውን ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎችና ለሽፍቶች ስንቅ አቀባዮችን ለህግ አሳልፈው ሊሰጡ ይገባል ብለዋል።

ለአብነት በቅርቡ ከወረዳው ከተዘረፉ 7 የጦር መሳሪያዎች 6ቱ ኩጃ ከተማ ላይ የተሸጡ መሆናቸውን ፖሊስ አረጋግጧል ብለዋል፡፡

ይህ እያለ ቀበሌዋም ሆነ ወረዳው ሰላም ሊሆን አይችልም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በሄኖክ ወ/ገብርኤል

ግንቦት 10 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *