በሕግ ማስከበር ስም የሚነሱ የሕዝብ ጥያቄዎችንና ጠያቂዎችን የማጥፋትና ሕዝባችንን አንገት የማስደፋት እንቅስቃሴ አጥብቀን እንቃወማለን!

(በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) የሕዝብ ተወካይ አባላት የተሰጠ መግለጫ፤)

ባለፉት አራት ዓመታት በሕዝባችን ላይ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚደርስበት ሁሉንአቀፍ ማንነትን መሰረት ያደረገ ጅምላ ጭፍጨፋ፣ መፈናቀል ቅርጹንና አድማሱን እያሰፋ ተባብሶ ቀጥሏል። ይባስ ብሎም ትሕነግ፣ የቤንሻንጉል ነጻ አውጭና ኦነግ ሸኔ የአማራን ሕዝብ ለማጥፋት ይፋዊ ጦርነት ከፍተው ሕዝባችን ኅልውናው አደጋ ላይ ወድቆ በጠላቶቹ ከበባ ሥር ይገኛል።

እኛ የአብን የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላትም መንግስት ትንሹን መንግስታዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣና የሕዝባችንን ደኅንነት እንዲያረጋግጥ ስንወተውት ቆይተናል። ሆኖም መንግስት ለማሳሰቢያችን ጀሮ ባለመስጠቱና ስጋታችንን ባለመጋራቱ ሕዝባችን ማንነትን መሰረት ላደረገ ጅምላ ጭፍጨፋ፣ መፈናቀልና ስደት ከመዳረጉም በላይ ከተሞቹና በዘመናት ሂደት ያፈራው ንብረት ወድሞ ለአካላዊና ሥነልቦናዊ ችግር ተጋልጦ ይገኛል። በዚህም ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ መፈናቀል ከዓለም ቀዳሚ እስከመሆን ደርሳለች፡፡

ይባስ ብሎም የዜጎችን ኹለንተናዊ ደኅንነት ማስጠበቅ፣ ሕግና ሥርዓትን ማንበርና የተሳለጠ አመራር መስጠት ያልቻለው መንግሥት ሕዝባችን በትሕነግና ምስለኔዎቹ ኅልውናው አደጋ ላይ በወደቀበት በአሁኑ ጊዜ በነቁ አማሮች ማለትም በአብን አባላትና አመራሮች፣ በፋኖ አባላትና አገራቸውንና ሕዝባቸውን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ባገለገሉ የጦር መኮነኖች ላይ ማንነትን መሰረት ባደረገ መልኩ የአፈና፣ የሕገ-ወጥ እስር እና የመንግስታዊ እገታ ሥራዎች ላይ መጠመዱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአብን የሕዝብ ተወካይ አባላትን አሳዝኖናል፡፡

መንግስት የሕዝባችንን ደኅንነት ለማረጋገጥና አገራዊ አንድነትን ለማንበር ከፖለቲካዊ ሴራ በጸዳ አኳኋን ሕግ ቢያስከብር እኛም ከመረጠን ሕዝብ ጋር ሆነን የምንደግፈው ቢሆንም አሁን እየተደረገ ያለው ግን ሕግ ማስከበር ሳይሆን በአማራ ሕዝብ የሚነሱ የሕዝብ ጥያቄዎችንና ጠያቂዎችን የማጥፋትና ሕዝባችንን አንገት የማስደፋት እንቅስቃሴ ነው።

ይኼን ጉዳይ ለሕዝባችን ክብር ካለን ጽኑ ፍቅርና ታማኝነት የተነሳ በቸልታ የማንመለከተውና ከሕዝባችን ጋር ሆነን የምንታገለው ያደረ አማራ ጠል እሳቤ ነው። በመሆኑም እኛ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአብን የሕዝብ ተወካይ አባላት መንግስት በሕግ ማስከበር ስም እያደረገ ባለው መንግስታዊ እገታና አፈና አሳሳቢነት ላይ ከተወያዬን በኋላ፦

፩. በአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን አባላትና አመራሮች፣ በፋኖ አባላት፣ በሕጋዊ ታጣቂዎችና ወጣቶች እንዲሁም አገራቸውንና ሕዝባቸውን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ያገለገሉ የጦር መኮነኖችንና የጸጥታ አመራሮች ላይ የሚፈጸመው መንግስታዊ እገታና ስወራ በአስቸኳይ እንዲቆምና በዚህ ሰበብ በማንነታቸው ብቻ የታገቱ አካላትም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁ እንጠይቃለን፡፡

፪. መንግስት በሕዝባችን ላይ እየፈፀመ ያለው ማዋከብ የታወቀ ጠላት የሚያደርገው ዓይነት ሲሆን ማዋከቡ በአስቸኳይ የማይቆም ከሆነ አገርና ሕዝብ በጉጉት የሚጠብቀው የአገራዊ ምክክር ከወዲሁ እንዲጨናገፍ የሚያደርግ ውጤት የሚያስከትል መሆኑን አጥብቀን ለማሳሰብ እንወዳለን።

፫. ሕግ ማስከበርን ሰበብ በማድረግ የፌደራል የፀጥታ መዋቅር በሕገ መንግሥቱ ለክልልና ለፌድራል ተለይቶ የተሰጠውን ኃላፊነት እና ሚና በደፈጠጠ መልኩ ክልሉን በሕገ-ወጥ መንገድ ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ሙከራ እንዲያቆም እና የክልሉ መንግስት በፌደራል መንግስቱ ለሚፈጸመው መንግስታዊ እገታና ስወራ ተባባሪ ከመሆን ወጥቶ የሕዝባችንን ሰላምና ደኅንነት እንዲያስከብር እየጠየቅን ጉዳዮቹን በሰላማዊ መንገድ በውይይት እንዲፈታ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

፬. በሕግ ማስከበር ሰበብ ከተሞችን የጦር አውድማ የማድረግና ንጹሐንን መግደል መንግስታዊ ሽብር በመሆኑ መንግስት የሚያደርገውን ይሄን ሕገወጥ የሽብር ሥራ በአስቸኳይ አቁሞ ሕዝባችንን በማወያዬት የሕዝብ ፍላጎቶችና ድምጾች እንዲሰሙ እንጠይቃለን፡፡

፭. መላው አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆችም መሰል መንግስት በአማራ ሕዝብ ላይ ያወጀውን መንግስታዊ ሽብርና ጦርነት እንዲያቆም መንግስት ላይ ጫና እንድታሳድሩ ለአማራ ሕዝብ ያላቸሁን አጋርነትም በተግባር እንዲያሳዩ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

፮. መላው የአማራ ሕዝብ በዚህ ፈታኝ ወቅት ውስጣዊ አንድነቱን እንዲያጠናክር እየጠየቅን በአማራ ስም የተደራጃችሁ ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች፣ ወጣቶች፣ ምሁራንና መላው ሕዝባችን የአማራ ሕዝብ ላይ የተጋረጠውን የኅልውና አደጋና ከበባ በመቀልበስ ልጆቹን እንዲጠብቅ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

አንድ አማራ ለሁሉም አማራ ፣ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!

ግንቦት 12 ቀን 2014 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ሸዋ፣ ኢትዮጵያ!

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *