ወቅታዊውን የከፋ የፖለቲካ ሁኔታ እያቀጣጠሉ ያሉ ግጭቶችንና የፖለቲካ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ ነን ያሉ ፖለቲካ ፓርቲዎች ‘‘የተቃዋሚ ፓርቲዎች ምክር ቤት ” ማቋቋማቸውን አስታወቁ፡፡

ከመንግስት እና አጋር ፓርቲዎች ጋር በሚደረገው ብሄራዊ የውይይት አቀራረብ ላይ ያለውን መሰረታዊ ልዩነት ተመልክተን እውነተኛ የዲሞክራሲ ስርዓትን የሚያስገኝ ሀገራዊ ውይይት አማራጭዎቻችንን ለማቅረብ ስንል የተቃዋሚ ፓርቲዎች ምክር ቤት ማቋቋማችን ይታወቅልን ብለዋል፡፡

በዚህ ምክር ቤት ውስጥ ሕብር ኢትዮጵያ፣ የአፋር ሕዝብ ፓርቲ፣ የአፋር ፍትህ እና ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፣ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር፣ የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ ዓረና ትግራይ እና የዶንጋ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት እንደሚገኙም ተነግሯል፡፡

ይህ የተቃዋሚዎች ምክር ቤት በመግጫው ‘‘ እኛ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ዋና ዋና ባለድርሻ አካላት የሆነው የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ፣ ወቅታዊውን የከፋ የፖለቲካ ሁኔታ እያቀጣጠሉ ያሉ ግጭቶችንና የፖለቲካ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሙሉ ቁርጠኝነት አለን። ” ሲል ገልጻል፡፡

ኢትዮጵያ የገባችበትን አሳሳቢ ሁኔታ በመረዳት ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚበጀው ብሔራዊ ውይይት መሆኑን እንደተስማሙም በመግለጫው አትቷል፡፡

መንግስት በፓርቲዎቹ አነሳሽነት ለሚደረገው ሀገር አቀፍ የውይይት ስልቶች እና ሂደቶች በተመለከተ ተደጋጋሚ ስብሰባዎችን አዘጋጅቷል፡፡
ነገር ግን ውይይቶቹ በሂደት ላይ ባሉበት ወቅት እና ባለድርሻ አካላት አገራዊ ውይይቱን ለማደራጀት የተሻለው መንገድ ላይ እየተከራከሩ ባሉበት ወቅት፣ መንግስት በአንድ በኩል ሂደቱን የሚቆጣጠር ረቂቅ ህግ በማዘጋጀት በአንድ ፓርቲ የበላይነት ባለው ፓርላማ በኩል የፖለቲካ ፓርቲዎችን ችግር ችላ በማለት አጽድቋል ሲልም ከሷል ።

አሁን ያለው መርዛማ የፖለቲካ ምህዳር ደም አፋሳሽ ጦርነቶችን ያስከተለው ኢኮኖሚያዊ ውድቀት እና መንግስትን ጨምሮ በሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች መካከል ያለው ልዩነት ሊፈታ የሚችለው ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተሟላ መልኩ በተሳተፉበት እና በእውነተኛ ሀገራዊ ውይይት ብቻ ነው የሚፈታው ብሎ ያምናል። በመፍትሔው ውስጥ ንቁ የመሳተፍ እድል እንዲደረግም ምክር ቤቱ ጠይቋል፡፡

ስለሆነም ዛሬ በፖለቲካ/በማህበራዊ እና በኢኮኖሚያዊ ገጽታ ላይ የተጋረጡ ዋና ዋና ጉዳዮችን ለመፍታት የታቀዱ ብሄራዊ ውይይቶች ሂደቱን የተሳካ እንዲሆን እድል ለመስጠት ቢያንስ የአለም አቀፍ ደረጃዎችን እና ተግባራትን ያሟሉ እንዲሆኑ ‘‘የተቃዋሚ ፓርቲዎች ምክር ቤት ” ሃሳብ እንደሚያቀርብ አስረድቷል።

‘‘የተቃዋሚ ፓርቲዎች ምክር ቤት ” ጨምሮ በመግለጫው በአፋጣኝ ትግራይ፣ አፋር እና አማራ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ፣ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል እና በሶማሌ ክልሎች ያለው ጦርነት ማቆም እና በአለም አቀፍ ደረጃ ክትትል የሚደረግበት የተኩስ አቁም በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንደደረግም ጠይቋል።

የኮሚሽኑ አባላትን ግልጽነት፣ ነፃነትና ሁሉን አቀፍነት ለማረጋገጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኮሚሽኑ ውስጥ ትርጉም ያለው ተሳትፎ በማድረግ በሂደቱና በምርጫ መስፈርት መሳተፍ እንዳለባቸው አሳስቧል።

በዚህ ውስብስብ በሆነ ሆኒታ እርስ በርስ በተሳሰረ ዓለም ውስጥ ኢትዮጵያ ደሴት ስላልሆነችና የምንወስነው ውሳኔ ሁሉ ለሌሎች አገሮች ጠቃሚ በመሆናችን ፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተውጣጡ ታማኝ፣ ገለልተኛ አስተባባሪዎች ወይም አስታራቂዎችን በብሔራዊ የውይይት ሂደት ውስጥ እንዲሳተፉ የሚፈቅድ አሰራርን እንጠይቃለን ብሏል።

በቂ የመተማመን እርምጃዎች፣ ለቁልፍ ተሳታፊዎች ደህንነት ከለላ፣ ውጤታማ አለምአቀፍ ቁጥጥር ፣ ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች መፍታት እና የምግብ እና የመድሃኒት እጥረት ለሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች ለማድረስ ሰብአዊ ርዳታ ላይ የተጣለውን እገዳ ማንሳት በቅድመ ሆኒታም ‘‘የተቃዋሚ ፓርቲዎች ምክር ቤት ” በመግለጫው አንስቷል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ግንቦት 29 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.