በአዲስ አበባ ስማርት ቆጣሪዎች ወደ ስራ እየገቡ ነዉ፡፡

ስማርት ቆጣሪዎችን ወደ ስራ ማስገባት የተጀመረዉ ለጊዜዉ ከፍተኛ የሃይል ተጠቃሚ ለሆኑ ኢንዱስትሪዎች ሲሆን በመድናዋ ብቻ ከ50 ሺህ በላይ የሚሆኑ ስማርት ቆጣሪዎች የመቀየር ስራ እንደተጀመረ ሰምተናል፡፡

መደበኛ ነበረውን ቆጣሪ ወደ ስማርት ቆጣሪዎች የመቀየር ስራ እየተሰራ መሆኑን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሚውኒኬሽን ዳሬክተር ከሆኑት አቶ መላኩ ታዬ ኢትዮ ኤፍ ኤም መረጃዉን አግኝቷል፡፡

አቶ መላኩ እንዳሉት ከፍተኛ በጀት ተይዞለት ወደ ስራ የገባው ነባሩን ቆጣሪ ወደ ስማርት የመቀየር ስራው ያስፈለገው፣ የሃይል መቆራረጥ ሲኖር ለመካታተል እና ከዚህ ቀደም ከቆጣሪ አንባቢ ጋር በተያያዘ የሚነሳውን ቅሬታ ይፈታል ተብሎ መሆኑን ነግረውናል፡፡

ይህ በፓይለት ደረጃ የተጀመረው ነባሩን ቆጣሪ የመቀየር ስራ፣ ኑርፍሌክስ በተባለ የየደቡብ ኮርያ ኩባንያ እየተከናወነ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ ወደ ተግባር የገባው አሰራር በመጀመርያው ዙር 5 ሺህ የሚሆኑ ቆጣሪዎችን የመግጠም ስራ እንደሚሰራ እና በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ 45 ሺህ የሚሆኑት ነባር ቆጣሪዎች የሚተኩ መሆናቸዉን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ለፕሮጀክቱ የገንዘብ ምንጭ የአለም ባንክ መሆኑን የተናገሩት አቶ መላኩ ፡- በብድር የተገኘው 12 ሚሊዮን 546 ሺህ 54 የአሜሪካ ዶላር ሲሆን፣ ቀሪው 9 ሚሊዮን 640 ሺህ 450 ብር ደግሞ በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን መሆኑ ነዉ የተገለጸዉ፡፡

መጋቢት 2/ 2014 ወደ ስራ የገባው ስማርት ቆጣሪዎችን የመቀየር ስራ፣ እስካሁን 107 የሚሆኑ ቆጣሪዎች መተከላቸውን ነግረዉናል፡፡

ይሁንና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ሲመጡ የመቀበል ልምዳችን ዝቅተኛ በመሆኑ፣ አገልግሎቱ ይህን የመቀየር ስራ ሲሰራ አንዳንድ የከፍተኛ ሃይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪ ባለቤቶች ስማርት ቆጣሪዎን ለማስቀየር ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ስራችንን እያጓተተው ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በረድኤት ገበየሁ

ግንቦት 30 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *