የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሶማሊያ በዝናብ ዕጥረት የተነሳ ከ200ሺህ በላይ ሰዎች ለረሀብ ተጋልጠዋል አለ፡፡

በድርቅ በተጎዳችዉ ሶማሊያ የምግብ ዋጋ በእጅጉ በመጨመሩ የተነሳ ዕሩብ ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ለከፋ ረሀብ መጋለጣቸዉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገልጿል፡፡

ለ4ኛ ተከታታይ የዝናብ ወቅት ዝናብ ያላገኘችዉ ሶማሊያ ፣የዓለም የዓየር ንብረት ሁኔታ እየዋለለ ባለበት በዚህ ወቅት፣ በዓመቱ መጨረሻላይም ከአማካይ የዝናብ መጠን በታች የሆነ ዝናብን ልታስተናግድ እንደምትችል ሜትሮሎጂስቶች እያስጠነቀቁ ይገኛሉ፡፡ይህም በ40 ዓመት ታሪክ ዉስጥ አስከፊ የተባለዉን ድርቅ እንድታስተናግድ እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ የረሀብ ቀዉስ እንዲከሰት አድርጓል ነዉ የተባለዉ፡፡

የህዝቡ ቁጥር በሚያዚያ ወር ከተጠበቀዉ ከሶስት ዕጥፍ በላይ የሆነ ጭማሪ ማሳየቱን የዓለም የምግብ ፕሮግራም፣ የምግብና ግብርና ድርጅት ፣ ዩኒሴፍ እንዲሁም የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኦቻ የገለጹ ሲሆን፣ በዚህም ቁጥሩ ወደ 213ሺህ ከፍ ማለቱ ነዉ የተገለጸዉ፡፡

ወደ 7 ነጥብ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ሶማሊያዉያን ከባድ የሆነ የምግብ ቀዉስ ዉስጥ ናቸዉ የተባለ ሲሆን፣ ይህም ማለት ማግኘት ከሚገባቸዉ አነስተኛ የካሎሪ መጠን እንኳን ማግኘት እንደማይችሉ እና በህይወት ለመቆየትም ንብረቶቻቸዉን መሸጥ ግድ እንደሚላቸዉ ነዉ የተገለጸዉ፡፡

‹‹ይህን ሰብዓዊ መቅሰፍት ለማቆም በፍጥነት መንቀሳቀስ አለብን ››ሲሉ የዓለም የምግብ ፕሮግራም የሶማሊያ ካንትሪ ዳይሬክተር ኤል-ኪዲር ዳሎም ተናግረዋል፡፡
‹‹ከተመጣጠነ ምግብ ዕጦት እና ከከፋ ረሀብ የተነሳ ቀድሞም ችግር ዉስጥ የነበሩ ዜጎችን አሁን በከፋ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፣ የግድ የቸነፈር እና ረሀብ አዋጅ እስኪወጣ መጠበቅ የለብንም፤ይህ ቸነፈርን ለማቆም ከጊዜ ጋር የምናደርገዉ ግብግብ ነዉ›› ሲሉም ያክላሉ፡፡

ከፈረንጆቹ 2021 አጋማሽ ጀምሮ በቀጠለዉ ድርቅ የተነሳ ሶማሊያዊያን ለስጋ፣ ወተት እንዲሁም ለገንዘብ ማግኛ ጥገኛ የሆኑባቸዉን ከ3 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ከብቶቻቸዉን ገብረዋል፡፡የረሀብ ተጎጂ በሆነዉ በተለይ በደቡባዊ ሶማሊያ የአልሸባብ ተዋጊዎች መኖራቸዉ ወደ ቦታዉ የሚደርሰዉን ዕርዳታ ከባድ ማድረጉም ነዉ የተገለጸዉ፡፡

‹‹ዓለምዓቀፉ ማህበረሰብ በተቻለዉ ፍጥነት ዕርዳታዉን እንዲያደርስ ጥሪያችንን እናቀርባለን፣አሁንም ግን በመላዉ ሶማሊያ ከፍተኛ የሆነ ቸነፈር ከመከሰቱ በፊት ለማቆም እንደምንችል ተስፋ አለን›› ሲሉ የምግብ እና እርሻ ድርጅት ተወካዩ ተናግረዋል፡፡

በ2011 በሶማሊያ ተከስቶ የነበረዉ ቸነፈር ዕሩብ ሚሊዮን አካባቢ ሰዎችን ህይወት መንጠቁ የሚታወስ ሲሆን፣ከሞቱት መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ዕድሜያቸዉ ከስድስት ዓመት በታች የነበሩ ህጻናት መሆናቸዉን አልጀዚራ በዘገባዉ አስታዉሷል፡፡

በእስከዳር ግርማ

ግንቦት 30 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *