ኤስ ኦ ኤስ የህጻናት መንደር ከ260ሺህ በላይ ዜጎች ተጣቃሚ የሚሆኑበት ፕሮግራም ይፋ አደረገ፡፡

በኢትዮጵያ ከተመሰረተ 48 አመታትን ያስቆጠረው ድርጅቱ፣ በሶስት ክልሎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ቀርጾ ወደ ስራ እንደገባም ነው የተገለጸው፡፡

ድርጅቱ በዋናነት በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ሰብአዊ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ቅድሚያ ሰጥቶ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታዉቋል፡፡
በኢትዮጵያ የኤስ ኦ ኤስ የህጻናት መንደር ዋና ዳረሬክተር አቶ ሳህለማርያም አበበ እንደተናገሩት፣ ፕሮጀክቱ 4 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በጀት ተይዞለታል ያሉ ሲሆን፣ ፕሮግራሙም በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

በፕሮጀክቱ መሰረት ሰሜን ሸዋ፣ ሰሜን ወሎ፣ አድዋ፣ መቀሌ እና ምስራቅ ሀረርጌ ዞኖች ተጣቃሚ እንደሚሆኑ ተነግሯል፡፡
የዚህ ፕሮጀክት ዋነኛ አላማ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸት ሲሆን፣ በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን የትምህርት ተቋማት መልሶ መገንባት ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶች እና ህጻናት ሰብአዊ ድጋፍ የሚያገኙበት ነው ሲሉ አቶ ሳህለማርያ አበበ ተናግረዋል፡፡

በሶስት ክልሎች ተግባራዊ ከሚደረገው 4 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 2.5 ሚሊዮን ዶላሩ በአማራ ክልል ብቻ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል፡፡
በፕሮጀክቱ ለገበሬዎች ዘር ከማቅርብ እስከ ለእርሻ የሚውሉ በሬዎች ድረስ ይቀርብላቸዋል ብለዋል ዳሬክተሩ፡፡

የምግብ አቅርቦት ችግር ላለባቸው እንደ ሰቆጣ ባሉ ሶስት ወረዳዎች የምግብ አቅርቦት ይፈጸማል ነው የተባለው፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የሲቨል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክትል ዳሬክትር አቶ ፋሲካው ሞላ እንደተናገሩት፣ ሀገሪቷ ለውጥ ካደረገችበት ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ የሲቭል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከፍተኛ ስራ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

ባለፉት ሶስት አመታት ከ 2 ሺህ በላይ አዳዲስ የሲቭል ማህበረሰብ ድርጅቶች መመዝገባቸውን ተናግረው፣ በሀገሪቱ በተከሰተው ጦርነት ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ባደረጉት ጥረት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

በአፋር እና በትግራይ ክልል ድርጅቶቹ ከ 440 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርገዋል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ኤስ ኦ ኤስ ኢትዮጵያ የህጻናት መንደር አሁን ላይ በሰባት ከተሞች 24 ያህል ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ በመድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡

በሔኖክ ወ/ገብርኤል

ሰኔ 01 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *