ባልታወቀ በሽታ ምክንያት ዶሮና እንቁላል ወደ ገበያ እንዳይገቡ ዕግድ ተጣለ፡፡

የግብርና ሚኒስቴር በአንዳንድ አካባቢዎች ያልታወቀ የዶሮ በሽታ ተከስቷል በማለት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ዶሮዎችና እንቁላሎች ከቅርብም ሆነ ከሩቅ አካባቢዎች ወደ ገበያ እንዳይገቡ ማገዱ ተሰምቷል፡፡

ከተለያዩ የክልል ከተሞች ወደ አዲስ አበባ፣ ከውጭ አገር የሚገቡና ወደ ውጭ ሊላኩ የነበሩ ከ20 ሺሕ እስከ 40 ሺሕ የሚደርሱ የተፈለፈሉ ጫጩቶችና እንቁላሎች ገበያ ውስጥ እንዳገቡ ክልከላ ተደርጓል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ሰኔ 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ለዶሮ አርቢዎችና ላኪ ድርጅቶች በጻፈው ደብዳቤ መሠረት ወደ አዲስ አበባ ሊገቡ የነበሩ፣ ወደ ውጭ የሚላኩ የተፈለፈሉ ጫጩቶች፣ እንዲሁም የደረሱ እንቁላሎች ለገበያ እንዳይውሉ በመታገዳቸው የዶሮ ዕርባታ ድርጅቶች ከፍተኛ ኪሳራ እያጋጠማቸው መሆኑን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር በደብዳቤው፣ ‹‹በተለያዩ ቦታዎች የዶሮ ሞት ክስተት እያጋጠመ በመሆኑ ችግሩ ተጣርቶ መፍትሔ እስከሚሰጥበት ድረስ የዶሮና የዶሮ ውጤቶች ገቢና ወጪ ላልተወሰነ ጊዜ ታግዷል፤›› ብሏል፡፡

በግብርና ሚኒስትር የኳረንቲን ኢምፖርት ኤክስፖርት ኢንስፔክሽንና ሰርተፊኬሽን ዳይሬክተር በሆኑት ዶ/ር ወንድማአገኝ ደጀኔ የተፈረመ ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፣ በዶሮ ዕርባታ የተሰማሩ ድርጅቶች የተጠቀሰውን ሕግ ተላልፈው ከተገኙ ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው ይጠቅሳል፡፡
ስለበሽታው መንስዔና አሁን ስለሚገኝበት ሁኔታ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት ዶ/ር ወንድምአገኝ ምላሽ መስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡
ከግብርና ሚኒስቴር ክልከላው ከተላለፈበት ሰኔ 3 ቀን በኋላ በርካታ በዶሮ ዕርባታ ዘርፍ ላይ ያሉ ድርጅቶች ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰባቸው መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ሰኔ 08 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *