የውጭ ማስታወቂያ ፈቃድ አሰጣጥ ስርዓትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ስታንዳርድ ይፋ ሆነ::

በመዲናዋ የውጭ ማስታወቂያ ፈቃድ አሰጣጥ ስርዓትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ስታንዳርድ ይፋ መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

ስታንዳርዱ በውጭ ማስታወቂያ ስራ ምርትና አገልግሎትን ለማስተዋወቅ ከከተማ ፕላን፣ ከአካባቢ ጥበቃና ደህንነት እና ከማህበረሰቡ ባህል፣ እምነትና አጠቃላይ እሴት በተጣጣመ መንገድ ፈቃድ የመስጠት፣ የመቆጣጠርና የማስተዳደር ስራን ለመስራት የሚያስችል ዘመናዊ አደረጃጀትና አሰራር ስርዓት መዘርጋት ያስችላል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ስጦታው አካለ የከተማዋን ውበትና ፅዳትን የማይጠብቁና የሚያበላሹ የውጭ ማስታወቂያዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም በተማከለ የህግ ማዕቀፍና የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲዘጋጁ ስታንዳርድ መዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም ከተማዋ በህገወጥ ማስታወቂያ ምክንያት ታጣው የነበረውን ኢኮኖሚያዊ ገቢ እና ማህበራዊ እሴቶችን ለማሰገኘት ያስችላል ብለዋል፡፡
ስንታንዳርዱ ለአገልግሎት ሰጭውም ሆነ ለተገልጋዩ ህብረተሰብ ግልጽ በማድረግ ቀልጣፋ፣ ውጤታማ እና ተጠያቂነት ያለበት የአሰራር ሥርዓት ለመዘርጋት እገዛ እንደሚያደርግም አስረድተዋል፡፡

በመዲናዋም ለውጭ ማስታወቂዎች ግልጋሎት የሚውሉ አካባቢዎች በተለያዩ ደረጃዎች መለየታቸውን ኢንጂነር ስጦታው ተናግረዋል፡፡
በስታንዳርዱ መሰረት የውጭ ማስታወቂያን በትምህርት፣ በጤና፣ በሀይማኖት እና በመንግስታዊ ተቋማት፣ በኤምባሲዎች፣ በአለም ዓቀፍ ድርጅቶች፣ በቤተመንግስት እና በመሳሰሉት ተቋማት አካባቢ መለጠፍ፣ መስቀል እና ማንጠልጠል አይፈቀድም፡፡

በመኪና፣ በባቡር እና በእግረኛ መሸጋገሪያ ድልድይ ምሰሶዎች ላይ ምንም አይነት የውጭ ማስታወቂያ መስቀል የተከለከለ ሲሆን ነገር ግን በድልድዮች ላይ መስቀል ይቻላል፡፡
በህንጻ የውጭ መስታወት በር፣ መስኮት እና የግንባታ ማጠናቀቂያ ቁሶች ላይ ምንም አይነት የውጭ ማስታወቂያ ማስተላለፍ አይቻልም፣ ሆኖም ግን በህንፃ ውስጥ ባሉ የፓርቲሽን መስታወት በር፣ መስኮት እና የግንባታ ማጠናቀቂያ ቁሶች ላይ በአከፋፈል ደንብ ቁጥር 117/2013 መሰረት በማስከፈል መፈቀድ ይቻላል፡፡

በማንኛውም ዘዴ የሚሰራጭ የውጭ ማስታወቂያ ከይዘት አኳያ ማናቸውንም ሕግ ወይንም መልካም ስነ ምግባር የማይፃረር፣ አሳሳች ወይንም ተገቢ ካልሆነ አገላለፅ ነፃ የሆነ፣ የህብረተሰቡን ማህበራዊና ባህላዊ እሴት የሚያከብርና የሸማቹን ህጋዊ ጥቅም የማይጎዳ መሆን ይኖርበታል፡፡
በሌላ በኩል የሚተዋወቀውን ምርት ወይንም አገልግሎት እውነተኛ ባህሪ፣ ጥቅም፣ ጥራትና መሰል መረጃዎችን የሚገልፅ፣ የሌሎችን ሰዎች ምርት ወይንም አገልግሎት የማያንቋሽሽ፣ የአገርን ክብርና ጥቅም የሚጠብቅ እና የሙያ ስነምግባርን የሚያከብር ይዘትና አቀራረብ ያለው መሆን አለበት፡፡
የማስታወቂያ ሰሌዳ በሚተከልበት ወይም በሚገነባበት ቦታ በቂ የፀሐይ ብርሃንና መተላለፊያ ያለው፣ የእግረኛና የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ የማይከለክል፣ የማያውክ፣ የማይገድብ እና ነጻ መሆን አለበት፡፡
ማንኛውም የውጭ ማስታወቂያ አስነጋሪ ድርጅት/ተቋም/ በአንድ በቦታ ላይ በተሰጠው ፈቃድ ሌላ አከባቢ/ቦታ/ መትከል አይቻልም፡፡
የውጭ ማስታወቂያ ከተሰቀለበት ሰሌዳ ወርድና ቁመት መትረፍ የሌለበት ሲሆን ለፈቃድ የሚቀርብ የውጭ ማስታወቂያ ይዘት በሀገሪቱ የስራ ቋንቋ መቅረብ ይኖርበታል፡፡
የውጭ ማስታወቂያ ሰሌዳ መጠን በሜትሪክ ሲስተምና በግራፊክ ስታንዳርድ መቅረብም ይገበዋል፡፡
የውጭ ማስታወቂያ ሰሌዳ በመስታወት የሚሰራ ከሆነ የመስታውቱ ውፍረት 6 /ስድስት/ ሚሊ ሜትር ሆኖ ቢሰበርም የማይረግፍ መሆን አለበት፡፡
በሌላ በኩል በኤሌክትሪክ የሚሰራ ዲጂታልና ባለብርሀን ማስታወቂያ ሳጥን /Light box/ የራሱ የኤሌክትሪክ መስመርና መቆጣጠሪያ ያለው መሆን ይኖርበታል፡፡

የመሰረተ ልማት አውታሮችን በማይጎዳና አግባብ ባለው አካል የተዘጋጀ የስትራክቸራል ውቅር ንድፍ በሚያቀርበውና በሚያዘው መስፈርት መሰረት ይወሰናል፡፡
በተያያዘ የወረቀትና ወረቀት ነክ ማስታወቂያ መለጠፊያ ቦርዶች ላይ ብቻ ካልሆነ በስተቀር በሌላ ቦታ ምንም አይነት ማስታወቂያ መለጠፍ አይቻልም፡፡

ውበቱ ሲጓደልና የውል ጊዜው ሲያልፍ በጨረታው ያሸነፈው ድርጅት ውሉን ካጠናቀቀ በኋላ ማስታወቂያውን አንስቶ ላዋዋለው አካል ማስረከብ ይኖርበታል፡፡
በድምፅ ማጉያ መሳሪያ ወይም በድምፅ ካሴት በመጠቀም ምርትንና አገልግሎትን ለማስተዋወቅ ግለሰቡ ወይም ድርጅቱ በአካባቢ ጥበቃ ባለስልጠን በኩል የድምፅ ስታንዳርድ ይሁንታ ሲያገኝ ፈቃድ ይሰጣል፡፡

የቋንቋ አጠቃቀምን በተመለከተ የማስታወቂያ ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 759/2004 አንቀጽ 21/3 የውጭ ማስታወቂያ በሀገር ውስጥ ቋንቋ ወይም ፊደል የተጻፈ መሆን ወይም በውጭ ቋንቋ ወይም ፊደል ጭምር የተጻፈ ሲሆን የሀገር ውስጥ ቋንቋው ወይም ፊደሉ ከውጭው ቋንቋ ወይም ፊደል አስቀድሞ ወይም ከላይ ሆኖ የተጻፈ መሆን አለበት፡፡

መረጃው:- በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን የኮሙዩኒከሽን ዳይሬክቶሬት ነው

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *