በአዲስ አበባ የሚገኙ የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች በናፍጣ እጥረት ምክንያት የስርጭት ሰዓትን ከመቀነስ እስከ ማቋረጥ የሚደርስ ስጋት ውስጥ መግባታቸዉን ተናገሩ፡፡

በአዲስ አበባ የሚገኙ የሬድዮ ጣቢያዎች በናፍጣ እጥረት ምክንያት ስርጭት እስከ ማቋረጥ የደረሰ ስጋት ውስጥ መግባታቸዉን ገልጸዋል፡፡

በፉሪ የሚገኘው የሬድዮ ዋና ማሰራጫ ጣቢያ አከባቢው ላይ እየታየ ባለው ከፍተኛ የሆነ የሃይል እጥረት፤ ሬዲዮ ጣቢያቸው ለስርጭት የሚጠቀሙት ጀኔሬተር መሆኑ ይታወቃል፡፡

ጄኔሬተር ለመጠቀም ናፍጣ ያስፈልገናል ያሉት የሬድዮ ጣቢያዎቹ ዋና የቴክኒክ ሃላፊዎች፤አሁን ካለው የነዳጅ ሽያጭ እገዳ ጋር በተያያዘ የናፍጣ እጥረት እየገጠመን በመሆኑ እና በቂ ናፍጣ ስለሌለን ስርጭት የማቆም ስጋት ውስጥ ገብተናል ብለዋል፡፡

የሸገር ሬድዮ የቴክኒክ ክፍል ሃላፊ አቶ ዳዊት ተስፋዬ እና የኢትዮ ኤፍ የኤም የቴክኒክ ክፍል ሃላፊ አቶ ዳንኤል ደበበ፣ ዋናው የስርጭት ጣቢያው በሚገኝበት ፉሪ ያለው ሃይል ችግር እንዲቀረፍልን ደጋግመን ብንጠይቅም እስካሁን መፍትሄ የሚሰጠን አላገኘንም ብለዋል፡፡

በዚህም የተነሳ የስርጭት ስራውን እያስኬድን ያለነው በጄኔሬተር ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከሰሞኑ በጀሪካንና በርሜል ናፍጣ ግዢ በመታገዱ ከከተማው ንግድ ቢሮ ደብዳቤ ይዘን ብንሄድም በፖሊሶች አናስቀዳችሁም ተብለን ተከለከልን ሲሉ የቴክኒክ ክፍል ሀላፊዎቹ ቅሬታቸዉን አቅርበዋል፡፡

“የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ለዚህ ምላሽ እንዲሰጠን ብንጠይቅም ይህ ጉዳይ ፖሊሶችን ነው የሚመለከተው የሚል ምላሽ ሰጥቶናል፤ ፖሊሶች ደግሞ ይህ ጉዳይ እኛን አይመለከተንም” ማለታቸውን ነግረውናል፡፡

ጉዳዩን አንዱ ወደ ሌላዉ እየገፋ መፍትሄ ልናገኝ አልቻልንም ይላሉ የቴክኒክ ባለሙያዎቹ፡፡
የሚዲያ ተቋማት ለህዝብ እና ለሃገር ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ እየታወቀ በዚህ ደረጃ ቸል መባሉ እንዳሳዘናቸዉም ጨምረዉ ገልጸዋል፡፡

“አሁንም ቢሆን የሚመለከተዉ አካል ትብብር ያድርግልን፤ካልሆነ ግን በናፍጣ እጥረት ሳቢያ ስርጭት እስከማቆም ሊደርስ የሚችል ችግር ዉስጥ እንገኛለን” ሲሉ የቴክኒክ ክፍል ሃላፊዎቹ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የኮሚዪኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደሴ ከፈለኝ በጉዳዩ ዙሪያ መረጃዉ እንዳልነበራቸዉ ገልጸዉ፣ባለስልጣኑ ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር በመተባበር ለመፍትሄዉ እንደሚሰራ ነግረዉናል፡፡

በመሳይ ገ/መድህን
ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *