እንደ ሰዉ የሚራመደዉ ዉሻ!

ዴክስተር ይባላል በአሜሪካ ኮሎራዶ የሚኖር የ 7 ዓመት ዉሻ ነዉ፡፡
የመኪና አደጋ በፊት እግሮቹ ላይ ጉዳት ካደረሰበት በኋላ፣ እራሱን እንደ ሰዉ መራመድ ያስተማረ ዉሻ በመሆኑ በአለም ዙሪያ ላሉ ሁሉ ማነቃቂያ የሆነ ዉሻ ነዉ ይሉታል፡፡

ገና ቡችላ ሳለ ከባለቤቶቹ ቤት አምልጦ በመዉጣት የትራፊክ መንገድ ላይ ገብቶ አደጋ ይደርስበታል፡፡ በጊዜዉ ባለቤቶቹ የፊት ለፊት እግሮቹ ከመጎዳታቸዉ በላይ መትረፉን ነበር የፈለጉት እና ለሌላዉ ጉዳቱ ብዙም ትኩረት አልሰጡትም ነበር፡፡

መንቀሳቀሻ እንዲሆነዉ ዊልቸር ገዝተዉ ቢያቀርቡለትም ዴክስተር ግን ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነዉ የተጠቀመዉ፤ በሁለት የኋላ እግሮቹ በደንብ መራመድ እንደሚችል ከተረዳ በኋላ የሚያስቆመዉ አልተገኘም፡፡ ከዛ በኋላ በመንደር ዉስጥ አንገቱን ወዲያ እና ወዲህ እያዞረ እንደሰዉ መራመዱን ተያይዞታል፡፡ ለብዙዎችም አነቃቂ ነዉ ተብሎለታል፡፡

ዴክስተር በእግር እርምጃ ከቀን ቀን እየተሻሻለ እና ለዉጥ እያመጣ ነዉ፣ አሁን ላይ ያለማንም አጋዥ በመንደር ዉስጥ ይራመዳል፡፡ የመንደሩ ታዋቂም ሆኗል፣ ሰዎች እሱን ለማየት ከየቤታቸዉ መዉጣት ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡
በብዙዎች ፊት ላይ ፈገግታን የሚጭረዉ ዴክስተር፣ ህይወት የቱንም ያህል ብትደቁሰንም ሁሌም ቢሆን ለመነሳት የተሻለ መንገድ እንዳለ ማሳያ ተደርጎ እየተጠቀሰ ነዉ ፡፡
አሳዳጊዉ ‹‹ ይችላል ብለን አላሰብንም ነበር፣ ነገርግን እንዲሞክር እድሉን ሳልሰጠዉ ልተወዉ አልፈለኩም ነበር›› ብላለች፡፡

የዴክስተር ጉዳይ ከብዙ በጥቂቱ የሚከሰት ቢሆንም ግን ልዩ አይደለም ሲል ሀሳቡን የሚያጠቃልለዉ ኦዲቲ ሴንትራል፣ ፌዝ የምትባል ሁለቱንም የፊት እግሮቿን ያጣች ዉሻ እራሷን በኋላ እግሮቿ መንቀሳቀስ አስተምራ ለብዙዎች አርአያ እና ምሳሌ በመሆኗ በስሟ ፋዉንዴሽን እንደነበራትም ያነሳል፡፡

በእስከዳር ግርማ
ሐምሌ 19 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *