አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የነዳጅ እና ጋዝ አምራቾችን ‹‹አይን ያወጣ ስግብግብነት›› አለባቸዉ ሲሉ ወቀሱ፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በነዳጅ እና ጋዝ አምራች ኩባንያዎች ላይ ልዩ ቀረጥ ሊጣልባቸዉ ይገባል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ዋና ጸሀፊዉ በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡት በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የጋዝ እና ነዳጅ ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት የማይገባ ትርፍ የሚያገኙ ኩባንያዎች በመበራከታቸዉ ነዉ፡፡

ከችግሩ እና ከዚህ ጦርነት ለማትረፍ መሞከር ‹‹ከሞራል ዉጭ›› የሆነ ጉዳይ ነዉ ሲሉ ገልጸዉታል፡፡

ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በነዳጅ እና ጋዝ ላይ ከፍተኛ እጥረት የተከሰተ ሲሆን፣ ይህም ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እንዲኖር አድርጎታል፡፡

በዚህ የተነሳ ለቤት ዉስጥ ፍጆታ የሚጠቀሙ ሰዎች በዋጋዉ ሲማረሩ ፣ ኩባንያዎች ግን ከፍተኛዉን ትርፍ እያገኙ መሆኑ ያሳዝናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ቢፒ የተሰኘዉ የነዳጅ ኩባንያ ከጦርነቱ በኋላ በ14 ዓመት ጊዜ ዉስጥ ከፍተኛ ነዉ የተባለዉን ትርፍ ያገኘ ሲሆን፣ ሼል ደግሞ ከሚያዚያ እስከ ሰኔ ያለዉ የትርፍ መጠኑ ሪከርድ ሆኖ መመዝገቡ ተገልጿል፡፡

አራቱ ከፍተኛ የሀይል አቅራቢ ኩባንያዎች ኤክሶን፣ሼቭሮን፣ሼል እና ቶታል ኢነርጂስ በአንድ ላይ 51 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝተዋል፤ ይህም ካለፈዉ ተመሳሳይ አመት ጋር ሲነጻጸር በሁለት እጥፍ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

‹‹ይህ አይን ያወጣ ስግብግብነት ምስኪኖችን እና አቅም የሌላቸዉን እየጎዳ በጋራ መኖሪያ የሆነ ቤታችንን እያፈረሰ ነዉ›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

‹‹ስለሆነም መንግስታት እነዚህ ኩባንያዎች የሚያገኙት ትርፍ ላይ ከፍተኛ ቀረጥ በመጣል ከዛ የሚገኘዉን ገቢ ከባድ ጊዜን እያሳለፉ የሚገኙ ምስኪኖችን እና አቅመ ደካሞችን እንዲረዱ እማጸናለዉ›› ሲሉ መናገራቸዉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በእስከዳር ግርማ
ሐምሌ 28 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *