የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ላይ ብቻ ሳይሆን ጥራት እና ደህንነት ላይ የበለጠ መስራት አለብን ሲሉ የተናገሩት የጤና ሚኒስቴር ድኤታዉ ዶክተር አየለ ተሾመ ናቸው።
ኢትዮጵያን ሶሳይቲ ኦፍ ኦርቶፔዲክስ ኤንድ ትራውማቶሎጂ “ከግጭት እና ጦርነት በኋላ የሚከሰቱ የአካልና የስነልቦና ጉዳቶችን ማከም “በሚል ጉባኤ አዘጋጅቷል።
እንደ ሀገር ሁሉን አቀፍ የጤና ተደራሽነትን ለማሳካት ከያዝነው ግብ አንፃር እየሄድንበት ያለነው መንገድ የተሻለ ነው ያሉት ዶክተር አየለ አሁንም ግን በየደረጃው ብዙ የሚጠበቁብን ስራዎች አሉ ብለዋል።

በተለይ ደግሞ የቀዶ ህክምና አገልግሎቶች ከዛም ከፍ ሲል የአጥንት ቀዶ ህክምናን ስናነሳ ምንም እንኳን አሁንም አለምአቀፋዊ ችግር ቢሆንም እንደ ሀገር ግን በጣም ወደ ኋላ ቀርተናል ነዉ ያሉት።
ተደራሽነት ላይ ከ100ሺህ ከሚጠበቅብን በ10 እጥፍ ወደ ኋላ ቀርተናል፣ እንደ ሀገር ብዙ ስራ መስራት ይጠበቅብናል ሲሉም አክለዋል።
ደህንነት እና ጥራት ላይ መስራትን በጣም ፈታኝ ከሚያደርጉት ጉዳዮች መካከል የህዝብ ፍላጎት እና ጥያቄ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር መሆኑም እንደ ምክንያት ተነስቷል፡፡
ዶክተር አየለ የማህበረሰብ ተኮር የጤና ኢንሹራንስ ህዝቡን የበለጠ አገልግሎት ጠያቂ እያደረገው ስለሆነ ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም ማጎልበት ይኖርብናል ሲሉም ተናግረዋል።
በእስከዳር ግርማ
ነሐሴ 19 ቀን 2014 ዓ.ም
