“የአማራ ባንክ “ጣና ዋንጫ”!

“ከባንክ ባሻገር “በሚል መሪ ቃሉ የባንክ ኢንደስትሪውን የተቀላቀለው አማራ ባንክ በስም ባለቤት ስፖንሰርነት ያዘጋጀዉን “የአማራ ባንክ “ጣና ዋንጫ” በባህርዳር ከተማ ስፖርታዊ ውድድር ሊያደርግ ነው።

“የአማራ ባንክ “ጣና ዋንጫ” በሚል ስያሜ የተሰጠው ስፖርታዊ ውድድሩ መስከረም 6 ቀን 2015 ዓ.ም ይጀምራል።

በዚህም ስፖርታዊ ውድድር ላይ የቤትኪንግ ፕሪሜርሊግ ተሳታፊ ቡድኖችን ጨምሮ ሁለት የኡጋንዳ ቡድኖች ተጋባዥ እንደሚሆኑ የአማራ ባንክ ማርኬቲንግ እና ብራንዲንግ ዳይሬክተር አቶ አስቻለው ታምሩ ተናግረዋል።

ባንኩ ከባንክ ባሻገር መሆኑን በተግባር እያሳየ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ባንኩ ማህበረሰቡን በአንድነት በሚያስተሳስሩ ጉዳዮች ላይ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ማህበረሰቡን በአንድ ከሚያቀራርቡ ተግባራት መካከል አንዱ ስፖርት በመሆኑ ይህን ስፖርታዊ ውድድር ለማድረግ መታቀዱን ገልፀዋል።

ውድድሩም በማህበረሰቡ ላይ ከሚፈጥረው መልካም መስተጋብር ባለፈ፣ ለባህርዳር ከተማ የቱሪዝም መነቃቃት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ተነስቷል።

ባንኩ በማህበረሰቡ መካከል በጎ መስተጋብርን ለመፍጠር “የአማራ ባንክ_ጣና ዋንጫ” በሚል ስያሜ የተሰጠውን ውድድር ለማድረግ ከባህርዳር ከተማ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ጋር የስምምነት ፊርማም አድርጓል።

ውድድሩ መስከረም 6/2015 ተጀምሮ መስከረም 14/2015 እንደሚጠናቀቅ በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

አማራ ባንክ ጨዋታውን በስም ባለቤት ስፖንሰርነት ሲያዘጋጅ ከስፖርቱ ፋይዳዎች ባለፈ የከተማዋንና አካባቢዋን ቱሪዝም በማነቃቃት ማኅበረሰቡ የሚያገኘውን ጥቅም ታላሚ በማድረግ ነው፡፡

የአማራ ባንክ ስራውን በጀመረበት ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም ነፃ የትራስፖርት አገልግሎቶትን ለአንበሳ ባስ ተጠቃሚዎች መስጠቱና በደም ልገሳ ፕሮግራሞች ላይ ሲሳተፍ መቆየቱ ይታወሳል።

በመሳይ ገ/መድህን

ጳጉሜ 03 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *