የ3.5 ሚሊዮን ብር ተሽከርካሪ በጨረታ አሸንፎ የወሰደው ግለሰብ ያቀረበው ሰነድ ሐሰተኛ ሆኖ በመገኘቱ በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡

ከ 3 ሚሊዮን 5 መቶ ሺህ ብር በላይ የዋጋ ግምት ያለው ተሽከርካሪ በጨረታ አሸንፎ የወሰደው ግለሰብ ያቀረበው ሰነድ ሲረጋገጥ ሃሰተኛ ሆኖ በመገኘቱ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።

ተጠርጣሪው ግለሰብ ወንጀሉን የፈፀመው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ለጨረታ ባቀረባቸው ተሽከርካሪዎች ላይ ተጫራች ሆኖ በመሳተፍ ነው፡፡

ጥቅምት 15 ቀን 2015 ዓ/ም በተካሄደው በዚሁ ጨረታ ላይ የተሳተፈው ተጠርጣሪው፤ ለማስያዥያነት በዳሽን ባንክ ስም የተዘጋጀ ሀሰተኛ ሲፒዮ እንዲሁም ጨረታውን ካሸነፈ በኋላ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መስቀል ፍላወር ቅርንጫፍ 3 ሚሊዮን 565 ሺህ ብር ገቢ ተደርጓል የሚል ሃሰተኛ ደረሰኝ ለድርጅቱ በማቅረብ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 2-B87869 አ/አ የሆነ ተሽከርካሪ ወስዶ ከአካባቢው መሰወሩን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል።

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ሰነድ የማረጋገጥ ስራ በሚሰራበት ወቅት ጨረታውን አሸንፎ ተሽከርካሪውን የወሰደው ግለሰብ ያቀረበውን ሰነድ ትክክለኛነት ተጠራጥሮ ለፖሊስ ካመለከተ በኋላ ፖሊስ ባደረገው ከፍተኛ ክትትል ግለሰቡን ከነተሽከርካሪው በቁጥጥር ስር በማዋል እና የሰነዱን ሃሰተኛነት በማረጋገጥ በህግ አግባብ ተጠያቂ እንዲሆን እየተሰራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።

ተቋማት በተለያዩ ምክንያቶች የሚቀርቡላቸውን ገንዘብን ተክተው የሚሰሩ እና ከገንዘብ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሌሎች ሰነዶች አስቀድመው በማረጋገጥ ሊፈፀምባቸው ከሚችል ወንጀል ራሳቸውን ሊከላከሉ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ መልዕክቱን አስተላልፏል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ህዳር 19 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *