በትግራይ ክልል የሚገኘው መሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ በቅርብ ቀናት ውስጥ ወደ ሥራ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

ፋብሪካው ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዞ ሥራ ማቆሙ የሚታወቅ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በማዕድን ሚኒስቴር አማካኝነት የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኝ መደረጉን የሲሚንቶ አምራቾች ማህበር ገልጿል፡፡

የማህበሩ ፕሬዘዳንት ኃይሌ አሰግድ እንደተናገሩት፤ መሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ በዓመት 20 ሚሊዮን ኩንታል ሲሚንቶ የማምረት አቅም ነበረው፡፡ ከዚህ ውስጥ እስከ 12 ሚሊዮን የሚደርሰው ወደመሃል አገር ይመጣ እንደነበር አክለዋል፡፡

በጣም አስፈላጊ የሆኑ መለዋወጫዎችን በአየር ትራንስፖርት እንዲደርስ በማድረግ በቅርቡ ሥራ ይጀምራል ያሉት ፕሬዘዳንቱ፣ አሁን የቀረው ከሰል ብቻ ነው ብለዋል፡፡ ፋብሪካው ለአንድ ወር 20 ሺሕ ቶን የድንጋይ ከሰል፣ ነዳጅና ሌሎች መለዋወጫ እቃዎች እንደሚያስፈልጉትም ጨምረው ገልጸዋል።

የፋብሪካው ወደ ሥራ መግባት በተለይም በአፋር፣ ጎንደር፣ ወሎና ትግራይ ያለውን የሲሚንቶ ምርት ፍላጎት ያሳካል ተብሏል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ታህሳስ 21 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.