ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ለገና በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ይህ በዓል መለያየት የጠፋበት፣ ኅብረትና አንድነት የጸናበት፤ መለኮትና ሥጋ፣ ህያውና ሟች፣ ዘላለማዊና ጊዜያዊ፣ ፈጣሪና ፍጡር፣ ሰማያዊና ምድራዊ፣ ምሉዕና ውሱን፣ በተዋሕዶ አንድ ሆነው አዲስ የምሥራች የተበሰረበት መሆኑን አንስተዋል፡፡

የልደቱ ብሥራት እረኞችን ከሜዳ፣ ሰብአ ሰገልን ከሩቅ ከምሥራቅ ወደ አንድ አምጥቷል፤ ሰዎችን ከምድር ጠርቷል፤ መላእክትን ከሰማይ አውርዷል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያውያን የነገዋን ኢትዮጵያ የተሻለች ለማድረግ ከዚህ የልደት ታሪክ ብዙ ትምህርት ብንወስድ ይጠቅመናል፤ ዛሬ እዚህም እዚያም የምናየው የመለያየትና የመጠፋፋት አባዜ የባህሪያችን አይደለም፤ የማናችንም ማንነት መገለጫ አይደለም።

ይህ የተዘራብን ክፉ ዘር ውጤት ነው፤ የውስጥ የውጭ ባዳ አንድ ሆነው የዘሩብን ዘር ውጤት ነው፤ ያለንበት ዘመን ዘሩ የተዘራበት ጊዜ አይደለም ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ።

የጠላታችን ዓላማ አንዳችንን ጠቅሞ ሌላችንን መጉዳት ሳይሆን ሁላችንንም ማጥፋት ነው። ዲያብሎስ መጀመሪያ አዳምና ሔዋንን አካሰሰ። ቀጥሎ ሰውን ከፈጣሪው ነጣጠለ። ከዚያ ሰውን ከመኖሪያው ከገነት አፈናቀለ።

እሾህና አሜከላ እንዲበቅል አድርጎ ሰውንና ምድርን አቆራረጠ። ቃየልን በአቤል ላይ አስነስቶ አስገደለው። ጠላታችን አንዱን ሕዝብ ከሌላው በማጋጨት አይቆምም፤ አንዱንም ሕዝብ እርስ በርሱም ያባላዋል።

ክልልን ከክልል፣ ዞንን ከዞን፣ ወረዳን ከወረዳ፣ ጎጥን ከጎጥ፣ ቤተሰብን ከቤተሰብ፣ ባልን ከሚስት፣ ልጆችን ከወላጆች እያባላ ዓለምን ሁሉ የግጭትና የጠብ ዐውድማ ማድረግ ነው ምኞቱ።

ስለዚህ ቆም ብለን እናስብ። መንገዱ ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የሚበጅ፣ ለሁላችንም በቅቶ የሚተርፍ፣ አዲስ ማንነትን ይዘን እንደገና መወለድ ነው። ታሪክ ማለፉ አይቀርም። ታሪክ መለወጡም አይቀርም።

ቁም ነገሩ የታሪክ ተከሳሽና ተወቃሽ ወይንስ ተዘካሪና ተሞጋሽ እንሆናለን? የሚለው ነው። ከሩቅ መጥተው መሲኹን እንደተገናኙት ጠቢባን ሰብአ ሰገል ታሪክ እንሠራለን ወይስ እንደ ሄሮድስ ታሪክን ለማጥፋት በንጽሐን ላይ ሰይፍ እናነሣለን? የሚለው ነው።

እንደ ቅዱሳን መላእክቱ ለአዲስ ታሪክ አዲስ የምሥራች እናበሥራለን ወይስ እንደ ዘመኑ የአይሁድ ልሂቃን ባለፈው ታሪክ ላይ ተተክለን የቀረበልንን ዕድል በንቀት እንገፋለን? የሚለው ነው።

የእነዚህን ጥያቄዎች ትክክለኛ መልስ ማግኘት፣ ኢትዮጵያ በአዲስ ልደት መንገድ እየተጓዘች የጌታችንንና የመድኃኒታችንን ልደት እንድታከብር ባለ በቂ ምክንያት ያደርጋታል ብለዋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ታህሳስ 28 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.