የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ህዝበ ውሳኔው ያለ ምንም ሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲከናወን ጥሪ አቀረበ፡፡

ዛሬ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሚገኙ ስድስት ዞኖች (ጋሞ፣ ወላይታ፣ ጎፋ፣ ጌዴኦ፣ ኮንሶ እና ደቡብ ኦሞ) እንዲሁም አምስት ልዩ ወረዳዎች (ቡርጂ፣ አማሮ፣ ባስኬቶ፣ ዲራሼ እና አሌ) በሚካሄደው ሕዝበ ውሳኔ የሰብአዊ መብቶችን ሁኔታ በሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የሚከታተል የባለሞያዎች ቡድን ወደ ስፍራው ማምራቱን ገልጧል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ እንዳሉት፣ ሕዝበ ውሳኔ የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶች ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሚስተናገዱበት እና ዜጎች በሕዝባዊ ጉዳዮች የመሳተፍ መብታቸውን የሚተገብሩበት አንደኛው ሂደት መሆኑን ገልፀዋል።

ዶ/ር ዳንኤል አክለውም ” ዜጎች ያለምንም መድሎ፣ ጫና እና ጣልቃ ገብነቶች በነጻነት ድምፅ መስጠት እንዲችሉ ሁሉም አካላት ግዴታቸውን እንዲወጡ” ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኮሚሽኑ ከሚካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ጋር ተያይዞ ሰዎች ለሚገጥሟቸው የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በነጻ የስልክ መስመር 7307 ላይ በመደወልም መረጃ እና ጥቆማዎችን ማድረስ እንደሚችሉም አስታውቋል፡፡

ዛሬ በተጀመረው የህዝበ ውሳኔ ምርጫ ላይ በህግ ጥሰት የአንድ ምርጫ ጣቢያ ድምፅ አሰጣጥ መቋረጡ መገለጹ ይታወሳል::

ምክንያቱ ደግሞ በምርጫ ጣቢያው ድምፅ በመስጠት ሂደት ወቅት የቀበሌ አስተዳደር ሀላፊዎች በሶርቶ 1 ምርጫ ጣቢያ በመገኘት 105 የሚሆን የግለሰብ ጊዜያዊ መታወቂያዎችን ድምፅ ለመስጠት ለተሰለፋ ዜጎች በማደል ህገ ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው በመገኘታቸው መሆኑ ተነግሯል፡፡

በአቤል ደጀኔ
ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *