በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በሚተዳደሩ ትምህርት ቤቶች፤ የኦሮምኛ ቋንቋ ትምህርት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ መሰጠት ተጀመረ።

የከተማይቱ ትምህርት ቢሮ የተጨማሪ ቋንቋ ትምህርቱን የሚሰጡ 2,600 ገደማ መምህራንን ለመቅጠር በሂደት ላይ መሆኑን አስታውቋል።

የብዝኃ ቋንቋ ስርዓተ ትምህርት በአዲስ አበባ በሚገኙ የመጀመሪያ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መተግበር የተጀመረው፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ባለፈው ጥር ወር ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ነው።

በዚህ ውሳኔ መሰረት በአማርኛ ቋንቋ ትምህርት በሚሰጥባቸው ትምህርት ቤቶች ኦሮምኛ በሁለተኛ ቋንቋነት እንዲሰጥ ይደረጋል።

የአፍ መፍቻቸው ኦሮምኛ ለሆነ እና በዚሁ ቋንቋ ለሚማሩ ተማሪዎች ደግሞ፤ አማርኛን እንደ ተጨማሪ ቋንቋ እንዲወስዱ ካቢኔው ወስኖ ነበር።

የኮተቤ ዩኒቨርስቲ ያካሄደውን ጥናት መሰረት በማድረግ እንደተላለፈ የተገለጸው ይህ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ውሳኔ፤ የአረብኛ እና ፈረንሳይኛ ቋንቋ ትምህርት ለዘጠነኛ እና አስረኛ ክፍል ተማሪዎች በምርጫቸው መሰረት እንዲሰጥ መወሰኑም በወቅቱ ተገልጿል።

ይህንን መሰረት በማድረግ የሀገር ውስጥ ተጨማሪ ቋንቋዎች ከሶስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች፤ አሁን ከተጀመረው የሁለተኛ መንፈቅ ዓመት ጀምሮ እንዲሰጥ መደረጉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አድማሱ ደቻሳ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ካሉት 786 የግል እና የመንግስት ትምህርት ቤቶች ውስጥ፤ 625 ያህሉ የኦሮምኛ ቋንቋን በተጨማሪነት ማስተማር መጀመራቸውንም አቶ አድማሱ ገልጸዋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

የካቲት 17 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *