በዓድዋ በዓል ላይ የጸጥታ ኃይሎች በፈጸሙት ድርጊት ተጠያቂ እንዲሆኑ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጠየቀ፡፡

በ127ኛው የዓድዋ ድል በዓል ላይ በመንግሥት የጸጥታ አካላት የተፈጠረውን ችግር አስመለክቶ ባወጣው መግለጫ፣ የጸጥታ ኃይሎች ከገደብ ያለፈ ድርጊት ፈጽመዋል ብሏል፡፡

በበዓሉ ላይ አላስፈላጊ ኃይል የተጠቀሙ እና ከመጠን ያለፈ እርምጃ የወሰዱ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች፣ በሕግ ተጠያቂ ከመሆናቸው በተጨማሪ በሕግ አስከባሪዎች መሰል አደጋዎች እንዳይከሰቱ አስፈላጊ ሥልጠና ማግኘት አለባቸው ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ፣ በበዓሉ ላይ የተከሰቱትን ክስተቶች አስመልክተው በሰጡት ሀሳብ፣ የጸጥታ ኃይሎች በዓሉን ለማክበር በወጣው ሕዝብ ላይ ከልክ ያለፈ አላስፈላጊ ድብደባ፣ አስለቃሽ ጭስ፣ ጥይትና ሌሎች ከመጠን ያለፉ እምጃዎችን መውሰዳቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተወሰደው እርምጃ በዕድሜ የገፉ አዛውንቶችና ህጻናት ሳይቀሩ ጉዳት ማስተናገዳቸውን ጠቅሰው፣ ቢያንስ አንድ ሰው መገደሉን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡

በርካታ ሰዎችም የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲሉ ኮሚሽነሩ አክለዋል፡፡

በምኒልክ አደባባይ የዓድዋን ድል ለማክበር፣ እንዲሁም በአቅራቢያው በሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን ሃይማኖታዊ በዓል ለማክበር የተሰበሰበው ሕዝብ በኃይል መበተኑን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

በሔኖክ ወ/ገብርኤል

የካቲት 24 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *