አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ዲጂታል የብድር አገልግሎት ጀመረ።

ባንኩ ለዲጂታል ብድር የሚውል 5 መቶ ሚሊየን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ መመደቡ ተገልጿል።

አንበሳ ባንክ “አለኝታ” የተሰኘ የዲጂታል የብድር አገልግሎት ነው ስራ ላይ ያዋለው።

የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ ዳንኤል ተከስተ ባንኩ አነስተኛ የዲጂታል ብድር አገልግሎት ስርዓትን በዛሬው ዕለት ወደ ስራ ማስገባቱን ገልፀው በደሞዝና በዕለት ገቢ ለሚተዳደሩ ዜጎች አገልገሎት የሚሰጥ መሆኑን አንስተዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም የዲጂታል ብድር አገልግሎቱ ያለ ምንም የንብረት ማስያዣ ዋስትና ሳያስፈልግ በባንኩ ሂሳብ ያለው ደንበኛ በአካል መቅረብ ሳያስፈልገው በእጅ ስልክ ብቻ አገልግሎቱን ማግኘት ይችላል ነው ያሉት።

የብድር አገልግሎቱ አለኝታ የደሞዝ ብድር፣ አለኝታ ለራይድና ለታክሲ ሹፌሮች፣ አለኝታ ለጥቃቅንና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ፣ አለኝታ ለኤሌክትሮኒክስ እና የቤት እቃ መግዣ እንዲሁም አለኝታ የፋይናንስ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው በሚል በአምስት ዘርፍ የቀረበ ነው።

በአሁኑ ሰአት ወደ ስራ የገባው አለኝታ የደሞዝ ብድር አገልግሎት ሲሆን ከደሞዝ እስከ ደሞዝ በመሀል የሚኖርን የገንዘብ ችግር ለመቅረፍ ደንበኞች ብድር ወስደው ክፍያ የሚፈፅሙበት ነው።

የብድር አገልግሎቱ ለመንግስት እና ለግል ድርጅት ሰራተኞች እንዲሁም ለሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ የሚሆን ሁሉንም አካታች የብድር አገልግሎት መሆኑም ተገልጿል።

ቀሪዎቹ አራት የብድር አገልግሎቶች ደግሞ በቀጣይ ወደ ስራ የሚገቡ ይሆናል የተባለ ሲሆን በተጨማሪም የሌሎች ባንክ ደንበኞችንም ተጠቃሚ ለማድረግ ስራዎች እንደሚጀመሩ ነው የተገለፀው።

በእስከዳር ግርማ

መጋቢት 25 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.