የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመነት ኤጀንሲ በዘርፉ የተስተዋሉ ችግሮችን ለማቅረፍ የዲጂታል መታወቂያ (Digital ID) ማዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡
ኤጀንሲው ለጣብያችን በላከው መግለጫ በየትኛውም ጊዜ እና ሰዓት የሞተር ብስክሌቱን አሁናዊ ሁኔታ ከማዕከላዊ ሲስተም በመውሰድ ለኤጀንሲው የትራፊክ ቁጥጥር ባለሙያዎች እና ለትራፊክ ፖሊስ አባላት መረጃ መስጠት የሚያስችል ነው ብሏል፡፡
አዲሱ ስራ ላይ የሚውለው የመንቀሳቀሻ ፈቃድ (Digital ID) ሞተር ብስክሌቱ በህጋዊ መንገድ የመንቀሳቀስ ፈቃድ የተሰጠው መሆኑን እና አለመሆኑን ለማረጋገጥ፤ ሞተር ብስክሌቱ በወንጀል የሚፈለግ መሆኑን እና አለመሆኑን ማረጋገጥ፤ ሞተር ብስክሌቱ ላይ የተገጠመው ጂ.ፒ.ኤስ በትክክል መስራት እና አለመስራቱን፤ የሞተር ብስክሌት የመንቀሳቀሻ ፈቃድ የታደሰ መሆኑን እና አለመሆኑን ለማረጋገጥ የሚያገለግል ሲሆን ከአሽከርካሪ እና ተሽከርካሪ ፈቃድ እና ቁጥጥር ባለስልጣን አመታዊ የሞተር ብስክሌት ቦሎ ለማውጣት እንደ ግዴታ መስፈርት ሆኖ የሚያገለግልም ይሆናል ተብሏል፡፡
የሞተረኛውን የወንጀል ሪከርድ፣ የሞተር ብስክሌቱን ህጋዊነት፣ መንቀሳቀሻ ፍቃዱ መታደሱን እንዲሁም ከፍጥነት ወሰን በላይ ሲያሽከረክሩ ማጣራት አይቻልም ነበር የተባለ ሲሆን የመንቀሳቀሻ ፍቃዱም በኤጀንሲው እንዲሰጥ በማድረግ የዲጂታል መታወቂያ (Digital ID) መተግበሪያ በማልማት ማእከል ካለው ሲስተም ጋር በማገናኘት የሞተረኛው መንቀሳቀሻ ፍቃዱ ላይ QR Code እንዲኖር በማድረግ የትራፊክ ተቆጣጣሪዎችና ትራፊክ ፖሊሶች በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ላይ በሚጫን መተግበሪያ ከላይ የተዘረዘሩትን ዝርዝር ጉዳዮች በቀላሉ መለየት ያስችላል ተብሏል፡፡
በቅርቡ በሞተር ብስክሌት ላይ አዲስ የሚተገበረው የዲጂታል መታወቅያ (Digital ID) የቁጥጥርና የክትትል ስራውን ከማእከል በመሆን ቀድሞ ከነበረው የተሻለ ስራ መስራት የሚያስችል መሆኑን ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡
በአቤል ደጀኔ
ሚያዝያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም
