በዲጂታል የነዳጅ ግብይት ስርዓቱ ከ 2 ቢሊየን ብር በላይ ግብይት መፈጸሙ ተነገረ፡፡

የነዳጅ ግብይት ሙሉ ለሙሉ ወደ ዲጅታል ስርዓት ለመቀየር በተጀመረው የትግበራ ሂደት እስከአሁን ድረስ ከ 2 ቢሊየን ብር በላይ ግብይት መካሄዱን የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን ለኢትዮ ኤፍኤም አስታዉቋል፡፡

የባለስልጣኑ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ወ/ሮ በቀለች ኩማ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ፣ የነዳጅ ግብይት በዲጂታል ስርዓት መተግበር ከተጀመረ ወዲህ ከ 2 ቢሊየን ብር በላይ ግብይት ተካሂዶበታል ብለዋል፡፡

በቤንዚን ከ990 ሚሊየን ብር በላይ ግብይት መፈጸሙን እና በናፍጣ ደግሞ ከ 1 ቢሊየን ብር በላይ ግብይት እንደተፈጸመ ነዉ የነገሩን ፡፡

ይህ ግብይት ከነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚዎች ዉጪ የተደረገ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት መሆኑንም ነዉ የገለጹት፡፡

ከሚያዚያ 16/2015 ጀምሮ የነዳጅ ግብይት በኤሌክትሮኒክስ መሆኑን ተከትሎ በአዲስ አበባ ባሉ ነዳጅ ማደያዎች ላይ መጨናነቆች ተከስተዉ እንደነበር አስታዉሰዋል፡፡
በተጨማሪም ሰዉ ሰራሽ ችግሮችም ሁኔታዉን እንዳባባሱት የገለጹት ወይዘሮ በቀለች፤ ባለስልጣኑ ቸድግሩን በአጭር ጊዜ ማስተካከል እንደቻለም አንስተዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ አንዳንድ ማደያዎች ያላቸዉን ሁሉንም የነዳጅ መቅጃ ማሽኖች ከመጠቀም ይልቅ ቁጥሩን ቀንሰዉ በመጠቀም በቂ አገልግሎት የማይሰጡ መኖራቸዉን ነግረዉናል፡፡

በእነዚህ ማደያዎች ላይ ቁጥጥር እና ክትትል በማድረግ እርምጃ መወሰዱንም ወይዘሮ በቀለች አስታዉቀዋል፡፡

የዲጂታል የነዳጅ ግብይት ከግንቦት 1 ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን ተከትሎ፤ በክልሎች ላይ ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይፈጠሩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እንደተሰሩም ሰምተናል፡፡

ከክልሎች እስካሁን የደረሱ ሪፖርቶች አንዳንድ ቦታዎች ላይ የኔትወርክ ችግር መኖሩን ከማሳየት በስተቀር፤ እንደ አዲስ አበባ የማደያዎች መጨናነቅ አለመፈጠሩን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም አሁን ካለዉ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት በተጨማሪ ከጅቡቲ ነዳጅ ወደ ኢትዮጵያ ሲጫን ጀምሮ ፣ ለየትኛዉ ማደያ ምን ያህል ሊትር ነዳጅ ተራገፈ የሚለዉን ጨምሮ ነዳጅ ማደያዎችስ የደረሳቸዉን ነዳጅ እንዴት ነዉ እየተጠቀሙት ያለዉ የሚለዉን በደንብ ሪፖርት የሚያደርግ የግብይት ስርዓት ለመዘርጋት ባለስልጣኑ ጅቡቲ ካለ የሚመለከተዉ አካል ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ነግረዉናል፡፡

በእስከዳር ግርማ
ግንቦት 08 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *