አካታች የፋይናንስ ስርዓት እንዲዘረጋ የሚያግዝ የዲጂታል አሰራር ይፋ ሆኗል።

በሃገራችን በየጊዜው የሚነሳውን አካታች የፋይናንስ ስርዓት ችግርን ለመቅረፍ የሚያስችል የዲጂታል አሰራርን መዘርጋቱን “ኤሊት ፊን ቴክስ ሶሉሽን” ገልጿል።

ኢ- ብድር የተሰኘው የዲጂታል ሲስተም በባንኮች መካከል ትስስርን በመፍጠር የስራ ፈጣሪ ወጣቶች እና ገበሬዎች በቀላሉ ብድርን ማግኘት እንዲችሉ እንደሚያደርግ “የኤሊት ፊን ቴክስ ሶሉሽን” ዋና ስራ አስፈፃሚ ከሆኑት አቶ አላዛር ሰለሞን ኢትዮ ኤፍ ኤም ሰምቷል፡፡

ይህም የዲጂታል ሲስተም ብድር ለማግኘት የሚፈጀውን ጊዜ በ60 በመቶ እንደሚቀንስ አንስተዋል።

በዲጅታል መተግበሪያው ወጣቱን እና ገበሬውን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ብድር ለገበሬው እና ለወጣቱ በሚል የተዘጋጀ ስርዓት እንዳለ ዋና ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።

በየጊዜዉ በሃገራችን የሚነሳው የአካታች ፋይናንስ ችግር ወጣቶችን እና ገበሬውን ከምርታማነት ውጭ አድርገው እንዳቆዩት የሚናገሩት አቶ አላዛር አሁን የተዘረጋው ሲስተም ይህን ይቀርፋል ብለዋል።

በሲስተሙ ገበሬውን በኢ-ብድር ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲያስችል የኤክስቴንሽን ባለሞያዎችን ወደ ክልል ከተሞች እየላኩ እንደሚገኙ አንስተዋል።

ይህንንም ለማሳከት በሚደረገው ሂደት ውስጥ ከግብርና ሚኒስትር እና ከብሔራዊ ባንክ ጋር በጋራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።

“ኤሊት ፊን ቴክስ ሶሉሽን” በትራንስፖርት ዘርፉ በኢ-ድራይቭ እንዲሁም በፋይናንስ እና በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፉ የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱንም ኢትዮ ኤፍ ኤም ከደረሱት መረጃዎች አረጋግጧል።

በመሳይ ገ/መድህን

ግንቦት 08 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *