በደራሼ ልዩ ወራዳ እያጋጠመ ያለውን ግጭት በእርቅ ለመቋጨት የፊታችን ቅዳሜ ቀጠሮ ተይዞለታል፡፡

አመራሮችን ጨምሮ በርካታ አርሶአደሮችን ለሞት ሲዳርግ የነበረው ግጭት በእርቅ ሊፈታ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

በደራሼ ልዩ ወረዳ ከዞን አደረጃጀት ጋር በተያያዘ ተነስቶ በነበረው ግጭት ምክንያት አርሶአደሮችን ፤አመራሮችን፤ልዩ ሃይላትን እና ንጹሃን ዜጎችን ሲያስገድል የነበረው ግጭት በእርቅ ሊፈታ ነው ተብሏል፡፡

አዲስ የተሾሙት የልዩ ወረዳው ዋና አስተዳደሪ አቶ ብርሃኑ ኩናሎ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት፣ ባለፈው አመት ከዞን አደረጃጀት ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ግጭት በርካታ ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል፡፡

የወረዳው ዋና አስተዳደር፤የወረዳው የእንስሳት እና አሳ ሃብት ቢሮ ሃላፊ እና ፤የወረዳው የሰላም እና ጸጥታ ጽ/ቤት ሃላፊ የነበሩ በግጭቱ ከተገደሉ አመራሮች መካከል ይገኙበታል፡፡

በተጨማሪም ልዩ ሃይላት እንዲሁም ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውን እና በርካታ ንብረት መውደሙንም አቶ ብርሃኑ ነግረውናል፡፡

አሁን ላይ ልዩ ወረዳው አንጻራዊ ሰላም ሰፍኖበታል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፣ ውስጣዊ እና ውጫዊ ችግሮችን በመፍታት ወደ ልማታዊ ተግባራት ለመመለስ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ውስጣዊ ችግሮችን በንግግር እና በእርቅ ለመፍታት የፊታችን ቅዳሜ ቀጠሮ ይዘናል ያሉም ሲሆን ፤ከአጎራባች ዞኖችን እና ወረዳዎች ጋር የሚደረገው የሰላም ሂደትም ይቀጥላል ብልዋል፡፡

በመሳይ ገ/መድህን

ሰኔ 14 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.