ኢትዮ ቴሌኮም እና የኦሮሚያ ክልል የገቢዎች ቢሮ የግብር እና ቀረጥ ክፍያዎችን በቴሌብር ለመፈጸም የሚያስችል ስምምነት አድርገዋል፡፡

በዚህ ስምምነት መሠረት የኦሮሚያ ክልል የገቢዎች ቢሮ የግብር አሰባሰብ ስርአቱን በዲጂታል ሲስተም የተደገፈ በማድረግ የዘመነ የግብር እና የቀረጥ አሰባሰብ ስርዓት ለመዘርጋት፣ ለደንበኞች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት፣ የሥራ ማስኬጃ ወጪንና ጊዜ ለመቆጠብ፣ የክፍያ ደረሰኝ ማጭበርበርን ለማስወገድ፣ ኢንቨስትመንትን ወደ ክልሉ ለመሳብ እና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሚያስችለው ይሆናል ተብሏል፡፡

ይህ አሰራር የግብር እና የቀረጥ ክፍያዎችን በወቅቱ ለመሰብሰብ ከሚኖረው ጉልህ ሚና ባሻገር፣ ዜጎች ጊዜ እና ገንዘባቸውን ቆጥበው ቀላል እና አስተማማኝ በሆነው የቴሌብር የሞባይል መተግበሪያ ወይም አጭር ቁጥርን *127# በመጠቀም ክፍያዎቻቸውን በቀላሉ ካሉበት ሆነው በመፈጸም የክፍያ ማረጋገጫ ደረሰኝ ወዲያውኑ ለማግኘት ያስችላቸዋል፡፡

ከኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ ጋር በመቀናጀት የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቱ ተግባራዊ ከመደረጉ አስቀድሞ በቂ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማከናወኑን የገለጸው ኩባንያው፣ ለክልሉ የገቢዎች ቢሮ ሰራተኞች የቴሌብር የአገልግሎት ክፍያ አሰባሰብ እና ተያያዥነት ስላላቸው ጉዳዮች አስፈላጊውን የስራ ላይ ስልጠና እንዲሁም ለደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠቱንም አብራርቷል፡፡

ኩባንያው በቅርቡ ከገቢዎች ሚኒስቴር እና ከጉምሩ ኮሚሽን ጋር በፈጸመው ስምምነት የከፍተኛ ግብር ከፋዮችን ግብር በወቅቱ ለመሰብሰብ እንዲሁም ወደ ሀገር ውስጥ ለሚገቡ ዕቃዎች የጉምሩክ ቀረጥ ክፍያን በቀላሉ መፈጸም የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ ማድረጉን አስታውሶ ከሌሎች ክልሎች ጋርም በተመሳሳይ የግብር ክፍያን በቴሌብር መፈጸም የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራን እንደሚገኝ ገልጿል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ሰኔ 15 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.